ቱርክ ታሪካዊውን ሙዚየም መስጂድ እንዲሆን ወሰነች

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይፕ ኤርዶዋን ታሪካዊው አያ ሶፊያ ሙዚየም ወደ መስጂድነት እንዲለወጥ የሚያስችል ውሳኔን በፊርማቸው አጸደቁ።

ቀደም ሲል የቱርክ ፍርድ ቤት ኢስታንቡል ውስጥ የሚገኘው ታሪካዊውና ታዋቂው የባሕል ማዕከል አያ ሶፊያ መስጂድ እንዲሆን የሚያስችል ብይን ሰጥቷል።

አያ ሶፊያ 1500 ዓመታት ታሪክ ያለውና ሲመሰረት ካቴድራል የነበረ ሙዚየም ነው። ከዚያም ኦቶማኖች ካቴድራሉን ወደ ሙዚየምነት ቀይረውት ነበር። ሥፍራው በሙዚየምነት የተመዘገበው በአውሮፓውያኑ 1934 ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የቅርስ ጥበቃ ወኪል ዩኔስኮ ቱርክ ድርጅቱን ሳታማክር ሥፍራውን ወደ መስጅድነት እንዳትቀይረው አሳስቦ ነበር።

እርምጃውን በተመለከተም የቱርኩ ፕሬዝደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ለውጥ ያስፈልጋል ሲሉ ይሞግታሉ።

ቱርክ ውስጥ ያሉ እስላማዊ ድርጅቶች ሥፍራው መስጅድ እንዲሆን ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር። መንግሥትና ሐይማኖት ይነጣጠሉ የሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ ይህንን እንቅስቃሴ ሲያወግዙ ከርመዋል።

ሙዚየሙን መስጅድ ሊያደርግ ይችላል የተባለውን ውሳኔ በርካታ ዓለም አቀፍ የሐይማኖት ድርጅቶችና ፖለቲከኞች ተቃውመውታል።

የምሥራቁ ዓለም ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኃላፊ ውሳኔውን ተቃውመውታል። ከበርካታ ሚሊዮን የኦርቶዶክስ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች የሚኖሩባት ግሪክም የቱርክን ሃሳብ ተቃውማለች።

የዘመናዊ ቱርክ መስራች ናቸው የሚባሉት ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ናቸው በ1934 ሥፍራው ሙዚየም እንዲሆን የፈቀዱት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቦታው ከእምነት ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። የትኛውም እምነት ተከታይ የሆነ ሰው በነፃነት የሚጎበኘው ነበር።

የቱርክ ከፍተኛ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት የሆነው 'ካውንስል ኦፍ ስቴት' ግን ዛሬ አርብ ባስተላለፈው ውሳኔ "ሥፍራው መስጅድ ሊሆን ይገባል፤ ይህን ሥፍራ ከዚህ ውጭ ለሌላ ዓይነት ጥቅም ማዋል ሕገ-ወጥ ነው" ሲል በይኗል።

የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የቱርክ ፍርድ ቤት አያ ሶፍያን በተለመከተ ላቀረበችው መፍትሄ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱ እንሳዘናት አስታውቃለች።

ቤተክርስቲያኒቷ የቱርክ ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔ ወደ ከፋ ክፍፍል የሚወስድ ነው ትላለች።