በሶሪያ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ይጨምራል የሚል ስጋት ተፈጥሯል

በሶሪያ ሰሜን ምዕራብ ግዛት፣ አብዛኛው አካባቢ በአማፂያን ቁጥጥር ስር ያለ ሲሆን የመጀመሪያው በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው መገኘት በተጨናነቀው የስደተኞች መጠለያ ቫይረሱ በፍጥነት ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት አጭሯል።

የእርዳታ ድርጅቶች ቡድን እንዳለው በቫይረሱ የተያዘው ዶክተር ሲሆን፣ ይሰራ የነበረውም በቱርክ ድንበር አቅራብያ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ነው ተብሏል።

ዶክተሩ በአሁኑ ሰዓት ራሱን ለይቶ ያለ ሲሆን ከእርሱ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች የመለየት ስራ እየተሰራ ነው።

ዶክተሩ ይሰራበት የነበረው ሆስፒታል መዘጋቱን በቱርክ የሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ለወራት የእርዳታ ድርጅቶች ቡድን በሰሜን ምዕራብ የስደተኞች መጠለያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላል እያሉ ሲያስጠነቅቁ ነበር።

ባለፈው ዓመት፣ የሶሪያ መንግሥት ኢድሊብን ለመቆጣጣር ሰፊ ጥቃት ከፍቶ ነበር።

ከባለፈው ሕዳር ር ጀምሮ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ መጠለያ ካምፑ የመጡ ሲሆን በስፍራው ተጨናንቀው ለሚኖሩት ሶሪያውያን ስደተኞች በቂ የሆነ የጤና ማዕከል፣ ንፁህ ውሃ እንዲሁም ባለሙያ አለመኖሩ ተገልጿል።

በመጠለያ ጣብያው ተጋላጭ የሆኑ ህብረተሰቦች መካከል ደካማ የጤና ስርዓት ባለበት ሁናቴ ቫይረሱ በፍጥነት ሊስፋፋ እንደሚችል ፍርሃት አለ።

ሶሪያ ውስጥ ከጎርጎሳውያኑ 2011 ጀምሮ በተቀሰቀሰ የእርስ በእርስ ግጭት ወደ ስድስት ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸው ይገለፃል።

ሶሪያ እስካሁን ድረስ 372 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን በምርመራ ስታረጋግጥ ከእነዚህም መካከል 14 ሰዎች ሞተዋል።

በሶሪያ የኮቪድ-19 ምርመራ የማድረግ አቅም ደካማ መሆን፣ በቫይረሱ የሚያዙና የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።