ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፑቲን 'አስመርዘውታል' የተባለው አሌክሴ ከገባበት ሰመመን ነቃ
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን በድፍረት በመተቸት የሚታወቀው አሌክሴ የነርቭ ስርዓትን በሚያውክ መርዝ ከተመረዘ በኋላ ከገባበት ሰመመን መንቃቱን የሕክምና ባለሙያው አስታወቀ።
ፑቲን እንዳስመረዙት የሚጠረጠረው ተቀናቃኛቸው አሌክሴ ናቫልኒ ወደ ጀርመኑ ዝነኛ ሻርሌት ሆስፒታል ከተዛወረ በኋላ ላይሞት ይችላል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነበር።
የሕክምና ቡድኑ በሰጠው መግለጫ ፖለቲከኛው የተመረዘው ናቪቾክ’ በሚሰኝ የነርቭ ስርዓትን በሚያውክ መርዝ እንደሆነ ገልጸው ነበር።
በፀረ-ሙስና ዘመቻቸው የሚታወቁት አሌክሲ በበረራ ላይ እያሉ ነው በአውሮፕላን ውስጥ ተዝለፍልፈው የወደቁት።
አውሮፕላኑን በድንገተኛ ሁኔታም ኦምስክ የሚባል ቦታ ለማረፍ መገደዱንም ቃለ አቀባይዋ ኪራ ያርሚሽ በትዊተር ገፃቸው አስታውቀዋል።
የጀርመን መንግሥት አሌክሴ ላይ የተፈጸመውን ድርጊት አጥብቆ እንደሚያወግዝ ገልጾ፤ ሩሲያ በአስቸኳይ ማብራሪያ እንድትሰጥ ጠይቆ ነበር። መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርክልም በጉዳዩ ላይ ከካቢኔ አባላቶቻቸው ጋር አስቸኳይ ስብሰባ መቀመጣቸው ይታወሳል።
በርሊን ውስጥ የሚገኘው የሕክምና ቡድኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሌክሴ ለመተንፈስ እገዛ ከሚያደርግለት ሜካኒካል ቬንትሌተር ቀስ በቀስ እንዲላቀቅ መደረጉን አስታውቋል።
'' ለሚደረግለት ህክምና ጥሩ ምላሽ እየሰጠ ነው። በመርዙ ምክንያት ሊደርስበት የሚችለውን የረጅም ጊዜ ጉዳት ግን አሁን ላይ ሆነን ማወቅ አንችልም'' ብሏል የህክምና ቡድኑ።
በተጨማሪም ዶክተሮች ከአሌክሴ ባለቤት ጋር በቅርበት እየተነጋገሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአሌክሴ ቃል አቀባይ ኪራ ያርማይሽ በትዊተር ገጿ ላይ ባሰፈረችው መልዕክት '' ስለ አሌክሲ አዲስ ዜና፤ ዛሬ አሌክሲ ከሰመመን እንዲነቃ ተደርጓል። ቀስ በቀስ ሙሉ በሙሉ ከቬንትሌተር እንዲላቀቅ ይደረጋል። ሰዎች ሲያናግሩትም ምላሽ መስጠት ጀምሯል'' ብላለች።
አሌክሴ ናቫልኒ ነሐሴ 15፣ ቶምስክ ከምትሰኝ የሩሲያ ከተማ ወደ ዋና መዲናዋ ሞስኮ እየበረረ ሳለ ከፍተኛ ሕመም ስለተሰማው አውሮፕላኑ በድንገት ኦምስክ፣ ሳይቤሪያ እንዲያርፍ ተገድዶ ነበር።
አሌክሴ አውሮፕላኑን ከመሳፈሩ በፊት በቶምስክ አውሮፕላን ጣቢያ ቁጭ ብሎ ሻይ ሲጠጣ የሚያሳይ ፎቶ ተለቆ ነበር።
ይህም ለህመሙ ምክንያት መመረዙ ነው የሚሉ ግምቶች በስፋት ተዛምቷል። የሩሲያ መንግሥት ግን ይህን ወቀሳ በተደጋጋሚ ሲያስተባብል ቆይቷል።
የተቃዋሚው አሌክሴ መመረዝ ከተሰማ በኋላ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርከልና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አገሮቻቸው ለአሌክሴ ሕክምና ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው በይፋ ገልጸው ነበር።
ሆኖም የሩሲያ መንግሥት በሆስፒታሉ በኩል ሰውየው ወደ አምቡላንስ ለመግባት አቅም የለውም በሚል ሕክምናውን ሲከላከሉ ነበር።
የአሌክሴ ሚስት በበኩሏ የሳይቤሪያው ሆስፒታል ታማሚው ባሏ ወደ ጀርመን እንዳይወሰድ እያዘገየ ያለው ወደሞት አፋፍ ከተጠጋ በኋላ እንደማይተርፍ ሲያውቁ ለመስጠት ነው በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ስታሰማ ነበር።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በበኩሉ ሩስያ ስለ ኖቪቾክ ፕሮግራሟ ለዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች መረጃ መስጠት አለባት ማለቱ የሚታወስ ነው።
የመብት ተሟጋቹ አሌክሴ ናቫልኒ መመረዙን ተከትሎ ነው ስለ ኖቪቾክ ነርቭ ኤጀንት (መርዛማ ኬሚካል) መረጃ እንድትሰጥ የተጠየቀው።
የኔቶ ጸሐፊ ጄንስ ስቶልበርግ አባላቱ ጥቃቱን አውግዘዋል ብለዋል። የመብት ተሟጋቹ በኖቪቾክ እንደተመረዘ “ማስረጃ አለ” ሲሉም አክለዋል።
ሩስያ ግን ለአሌክሴ ሕክምና እያደረገ ያለው ሆስፒታል የሰጠውን ማብራሪያ አጣጥላለች።
ከጥቂት ወራትም በፊት የህገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ ድምፅ ይሰጥ መባሉን ተከትሎ ህገ መንግሥቱን የጣሰ ነው በማለት ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር አመሳስለውታል።
ፖለቲከኛው ይህንን ያሉት ማሻሻያው የአገሪቱን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ እንዲያስችላቸው የሚያደርግ በመሆኑ ነው።
በተለይም በአገሪቱ ውስጥ ያለ ቅጥ የተንሰራፋውን ሙስና በማጋለጥ የህዝብ ቀልብ የሳቡት ፖለቲከኛው የፕሬዚዳንት ፑቲን ዩናይትድ ራሺያ (የተባበረች ሩሲያ) ፓርቲን "ሌቦችና ቀማኞች" ሲሉም ይጠሯቸዋል።
በጎርጎሳውያኑ 2011 የፑቲን ፓርቲ ምርጫን አጭበርብሯል በማለት ከፍተኛ ተቃውሞ ማስተባበራቸውን ተከትሎም ለአስራ አምስት ቀናት ታስረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በ2013ም ገንዘብ አጭበርብረዋል በሚል ክስ ለአጭር ጊዜ ታስረው የነበረ ቢሆንም እስሩ ፖለቲካዊ ነው በሚል በከፍተኛ ሁኔታ ተወግዟል።