ፑቲን 'አስመርዘውታል' የተባለው አሌክሴ ለህክምና ወደ ጀርመን ተወሰደ

የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን በድፍረት በመተቸትና በማብጠልጠል የሚታወቀው የተቃዋሚ መሪ አሌክሴ ናቫልኒ ለህክምና ጀርመን ገባ።

አሌክሴ ለህክምና ወደ ጀርመን እንዲሄድ የሩሲያ ሃኪሞች ቀደም ሲል ተስማምተው ነበር።

አሌክሴ ከትናንት ጀምሮ ‹ነፍስ ውጪ-ነፍስ ግቢ› ላይ ይገኛል። የአሌክሴ ደጋፊዎች እና ቡድን አባላት አሌክሴ ከሻይ ጋር ተቀላቅሎ በተሰጠው መርዝ መመረዙን ይናገራሉ።

የሩሲያ መንግሥት ባለስልጣናትም ይህን ወንጀል ለመሸፋፈን እየሞከሩ ነው ሲሉ ይከሳሉ። ቀደም ሲል አሌክሴን ሲያክሙ የነበሩ የሩሲያ ሃኪሞች አሌክሴ በጠና በመታመሙ በአየር አምቡላንስ ተጭኖ ወደ ጀርመን የመሄድ አቅም የለውም በማለት ከሩሲያ መውጣት እንደማይችል ተናግረው ነበር።

አሌክሲን እያከሙ ከሚገኙት የሩሲያ ዶክተሮች አንዱ ‹‹አሌክሴ ወደ አምቡላንስ ለመግባት የሚሆን አቅም የለውም›› ሲሉ ትናንት ተናግረው ነበር። የአሌክሴ ቤተሰቦችና ደጋፊዎች ግን አሌክሴ ከሳይቤሪያ ሆስፒታል ካልወጣ እንደሞተ ይቆጠራል ብለው ነበር።

ጀርመን እና ፈረንሳይ ተቃዋሚውን ለማከም ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ አሌክሴን ወደ ጀርመን ለመውሰድና በጠና የታመሙ ሰዎችን ለማከም በሚረዱ መሳሪያዎች እና ባለሙያዎች የተሟላች የአየር አምቡላንስ ሩሲያ የደረሰችው ትናንት ነው።

አሌክሴን የጫነችው አውሮፕላን ዛሬ ጠዋት በርሊን ደርሳለች።

ቀደም ሲል ጀርመን የጤና ባለሙያዎች አሌክሴ ያለበትን ሁኔታ ከተመለከቱ በኋላ አሌክሴን ወደ ጀርመን ይዘው የመሄድ ‘’አቅምም ፍላጎትም’’ አለን ማለታቸው ተነግሯል።

አሌክሴ አውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ በሚገኝ አንድ ካፌ ውስጥ ያዘዘው ሻይ ላይ መርዝ ሳይሰጠው አልቀረም ተብሏል። አውሮፕላን ውስጥ እንደገባ ነው ተዝለፍልፎ የወደቀው።

አሌክሴ ናቫልኒን ምንድነው የሆነው?

አሌክሴ ፑቲን የሥልጣን ዘመናቸውን ማራዘማቸውን ሲተች ነበር።

ሕገ መንግሥቱን ጥሰዋል፣ ሥልጣን ማራዘማቸው መፈንቅለ መንግሥት ከማድረግ አይተናነስም ሲል ነበር። ትናንት ከቶምስክ ወደ ሞስኮ እየበረረ ሳለ ከፍተኛ ሕመም ስለተሰማው አውሮፕላኑ በድንገት ኦምስክ፣ ሳይቤሪያ እንዲያርፍ ተገዷል።

በ2011 ያቋቋመው ድርጅቱ የጸረ ሙስና ፋውንዴሽን ቃል አቀባይ ኪራ ያርሚሽ ‹‹አሌክሴን መርዝ አጠጡት›› ሲሉ በትዊተር ገለጹ።ይህን ተከትሎ አሌክሴ በቃሬዛ ከአውሮፕላን ወጥቶ ወደ አምቡላንስ ውስጥ ሲገባ የሚያሳይ ቪዲዮ ተለቀቀ።

ሌላ ቪዲዮ ደግሞ አሌክሴ አውሮፕላን ውስጥ ሳለ በከፍተኛ ስቃይ ሲጮኽ የሚያሳይ የሚረብሽ ምስል ተለቀቀ። ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ አሌክሴ በቶምስክ አውሮፕላን ጣቢያ ቁጭ ብሎ ሻይ ሲጠጣ የሚያሳይ ፎቶ ተለቀቀ። አሁን የሚገኝበት ሆስፒታል በሩሲያ የጸጥታ ኃይል የተከበበ ሲሆን ፖሊስ ከሆስፒታል የሱ የሆኑ ንብረቶችን ይዞ ሄዷል።

አሁን አሌክሴ በቬንትሌተር ነው የሚተነፍሰው፣ ራሱን ሙሉ በሙሉ ስቷል፣ ጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛል። ባለቤቱ ዩሊያ ናቫለናያ መጀመሪያ ወደ ሆስፒታሉ እንዳትገባ ተከልክላ ነበር።

ምክንያቱን ስትጠይቅም ታማሚው አልፈቀደም የሚል መልስ ተሰጥቷት ነበር። በኋላ ግን ገብታ እንድታየው ተፈቅዶላታል። በክሬምሊን ይደገፋሉ የሚባሉ ሚዲያዎች አሌክሴ ባለፈው ሌሊት መጠን ሲጠጣ ነበር የሚል ዜና የለቀቁ ሲሆን ባለቤቱ ግን ይህ የተቀነባበረ ነጭ ውሸት ነው፤ ወንዝ ወርዶ ሲዋኝ ነበር ያመሸው ብላለች።

አሌክሲ ናቫልኒ ማን ነው?

አሌክሴ በሩሲያ ውስጥ እውቅና ያገኘው የባለሥልጣናትን ሙስና በማጋለጥ ነው። በዚህም በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጓል። የፑቲንን ፓርቲ የሞሉት ሸፍጠኞችና ሌቦች ናቸው ይላል አሌክሲ።

በ2011 የፑቲን ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ምርጫ አጨበርብሯል ብሎ በማጋለጡ ለ15 ቀናት ታስሮ ነበር። በ2013 አሌክሴ በሙስና ክስ ተመስርቶበት ለአጭር ጊዜ ከታሰረ በኋላ ተለቋል።

በ2018 ፑቲንን ለመገዳደር ምርጫ ቅስቀሳ ቢጀምርም ቀደም ሲል በነበረበት የምዝበራ ክስ ምክንያት መወዳደር አትችልም በሚል ታግዷል። በ2019 ፑቲንን የሚቃወም ትልቅ ሰልፍ በመጥራቱ ሕገ-ወጥ የሰልፍ ጥሪ አድርገሀል በሚል ለ30 ቀናት ታስሯል።

ያን ጊዜ በእስር ላይ ሳለ ባልተለመደ ሁኔታ ሕመም ገጥሞት ነበር። ሐኪሞች የቆዳ አለርጂ የሚመስል ነገር ቢጠቅሱም እሱ ግን አለርጂ ኖሮበት እንደማያውቅ ተናግሮ ነበር።

በኋላ ላይ ግን የገዛ ሐኪሞቹ ለአንዳች መርዝነት ላለው ነገር ተጋልጠህ ነበር ሲሉ ነግረውታል።ምናልባት እስር ቤት ሳለ እሱን መርዞ ለመግደል ሙከራ ተደርጎ እንደነበር ይገመታል።

ቪላድሚር ፑቲን ከዚህ ቀደም በርከት ያሉ ተቃዋሚዎቻቸውን፣ የስለላ መኮንኖችን፣ ጋዜጠኞችን በጠራራ ጸሐይ በማስገደል እና በሰው አገር ጭምር ሄደው በመመረዝ ስማቸው ይነሳል።