ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ካሊፎርኒያ የሰደድ እሳቱን ለማጥፋት የአውስትራሊያን እርዳታ ጠየቀች
የአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት ራስ ምታት የሆነባትን ሰደድ እሳት ለመዋጋት 12ሺህ የሚደርሱ የእሳት አደጋ ሰራተኞችን ብታሰማራም እስካሁን እሳቱ በቁጥጥር ሥር አልዋለም።
ይልቁን የስድስት ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።
እሳቱ ጫካዎችንና እና ቤቶችን እያወደመ እንደሆነ የገለጹት የካሊፎርኒያ ግዛት አስተዳዳሪው ጋቪን ኒውሰም አደጋውን መቆጣጠር ከብዶናል ብለዋል።
ከተለያዩ የአሜሪካ ክፍሎች እርዳታ እየመጣ እንደሆነም ገልጸዋል። አክለውም አውስትራሊያ እና ካናዳም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
''እሳቱ የሰው ኃይል አቅማችንን እያዳከመብን ነው'' ብለዋል ገዢው።
እዚም እዚያም እየተከሰቱ የሚገኙት 560 የሰደድ እሳቶች ግዛቲቱ ከዚህ ቀደም ካስተናገደቻቸው መካከል ይህ መጠኑ ሰፊ መሆኑ ተገልጿል። በካሊፎርኒያ ያለው ከፍተኛው ሙቀት የሰደድ እሳቱን እያባባሰ መሆኑ ተነግሯል።
አርብ ዕለት የድንገተኛ አደጋ ክፍል ኃላፊዎች እንደገለጹት በአንዳንድ አካባቢዎች የእሳቱ መጠን በእጥፍ እየጨመረ ሲሆን በዚህም ምክንያት 175ሺህ ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ጨምሮ እስካሁን በሰደድ እሳቱ 43 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ግንባታዎች ደግሞ እንዳልነበሩ ሆነው መውደማቸው ተገልጿል። በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ ህንጻዎች አደጋ ላይ ናቸው።
እሳቱ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ ምቹ አለመሆኑ ደግሞ የማጥፋትና የመከላከል ስራውን በእጅጉ ፈታኝ አድርጎተል። በተጨማሪም በአካባቢው ያለው ከፍተኛ ንፋስ ነገሮችን ከባድ አድርጎባቸዋል።
እሳቱን ለመቆታጠር እስካሁን በርካታ እሳት አደጋ ሰራተኞች፣ መኪናዎችና አውሮፕላኖች ወደ አካባቢው የተንቀሳቀሱ ሲሆን እንደ ኦሪጎን፣ ኒው ሚክሲኮ፣ እና ቴክሳስ ያሉ ግዛቶችም ድጋፋቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።
የካሊፎርኒያ ገዢው ባስተላለፉት የእርዳታ ጥሪ ላይ ''በዓለማችን ቁጥር አንድ የሰደድ እሳት ተከላካይ ሠራተኞች'' ያሏት አውስትራሊያ ድጋፍ ታድርግልን ሲሉ ተማጽነዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የግዛቲቱ ነዋሪዎች የአየሩ ደህንነት እስካሁን ስላልተረጋገጠ ከቤታችሁ ባትወጡ ይሻላችኋል እየተባሉ ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ግዛቲቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግርም አጋጥሟታል።
በካሊፎርኒያ በሚነሳው ተደጋገሚ እሳት እስካሁን በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከሁለት ዓመት በፊት በተከሰተው የሰደድ እሳት ቢያንስ 25 ሰዎችን መሞታቸው የሚታወስ ነው።
ባሳለፍነው ዓመት ጥቀምት ላይ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ የሎስአንጀለስ ኗሪዎች መኖሪያቸውን ጥለው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበረ።