በምሥራቅ ባሌ የተመረዘ ውሃ የጠጡ 100 ፍየሎች ሞቱ

የሞቱ ፍየሎች

የፎቶው ባለመብት, HASANNUR IBRAHIM

በምሥራቅ ባሌ ዞን የተመረዘ ውሃ የጠጡ ከ100 በላይ ፍየሎች ሲሞቱ ስምንት ሰዎች ደግሞ ታመው ህክምና እርዳታ ማግኘታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለፁ።

በዞኑ ራይቱ ወረዳ በሃረዱቤ ገበሬ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ከ500 በላይ የሚሆኑ ፍየሎች የተመረዘ ውሃ ጠጥተው ከመካከላቸው 102 ሲሞቱ አራት መቶዎቹ መትረፋቸውን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።

የቀበሌው ነዋሪ የሆኑት አቶ ኡመር አብዱላሂ አካባቢው በረሃማ በመሆኑ ለሰዉም ሆነ ለእንስሳት ለመጠጥ የሚውለው ውሃ ከጉድጓድ የሚቀዳ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ውሃውን ከጥልቅ ጉድጓድ በገመድ እየጎተቱ በማውጣት እንደሚጠቀሙ የሚናገሩት አቶ ኡመር "ከድሮ ጀምሮ በእንደዚህ መንገድ ነው የምንጠቀመው፤ ቅርብ ጊዜ ግን አይተን በማናውቀው መልኩ 97 ፍየሎች ውሃውን እንደጠጡ ወዲያውኑ ሞቱ" ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

አምስቱ ፍየሎች ደግሞ የእንስሳት ህክምና ማዕከል ደርሰው መሞታቸውን ነዋሪው አክለው ተናግረዋል።

ከፍየሎቹ ውጪ ከጉድጓዱ ውሃውን የጠጡ ስምንት ሰዎች ታምመው እንደነበር ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።

ስምንቱ ሰዎች በአካባቢው በሚገኝ ጤና ተቋም ህክምና እርዳታ አግኝተው በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ለቢቢሲ የተናገሩት አቶ ኡመር፣ ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት ችግር ገጥሟቸው እንደማያውቅ አስረድተዋል።

አቶ ኡመር ለችግሩ ምክንያት ይሆናል የሚሉት ሁለት ነገር መሆኑን በማስረዳት፣ "አንደኛ መርዛማ አውሬዎች፤ እንደ እባብ ያለ ውሃ ውስጥ ገብቶ ሊሆን ይቸላል፤ ሌላኛው ደግሞ ድንበር ላይ ነው የምንኖረው፤ በዚህ ውሃ ላይ ደግሞ በተደጋጋሚ ግጭቶች አሉ፤ ምናልባት ሰዎች መርዘውት ሊሆን ይችላል" የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የራይቱ ወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሽብሩ አደሬ ስለሁኔታው ተጠይቀው፣ የጉድጓድ ውሃው እንዴት እንደተመረዘ ለማጣራት ናሙና ለአሰላ የእንስሳት ቤተ ሙከራ መላኩን ገልፀዋል።