ዶናልድ ትራምፕ ሻወር ቤት ውሃ ቀነሰብኝ ብለው አማረሩ

የአሜሪካ መንግሥት የገላ መታጠብያ ቧንቧ ጭንቅላት ምን ያህል ውሃ ማፍሰስ አለበት የሚለውን ደንብ ለመቀየር እያጤነ ነው፡፡

ይህን ደንብ ለማጤን የተገደደው ደግሞ ከሕዝብ በመጣ ቅሬታ ሳይሆን በዶናልድ ትራምፕ ጸጉር የተነሳ ነው፡፡

የ1992 የአሜሪካ በተደነገገ ሕግ የአሜሪካ የሻወር ቧንቧዎች ጭንቅላት በደቂቃ ከ2.5 ጋሎን በላይ እንዳያፈስ ያስገድዳል፡፡

ይህም ብክነትን ለመከላከል የወጣ ደንብ ነው፡፡

የትራምፕ አስተዳደር ይህንን መጠን ለመጨመር ይሻል፡፡ ምክንያቱም ትራምፕ ገላዬን ስታጠብ በቂ ውሃ እየፈሰሰልኝ አይደለም ሲሉ ቅሬታ በማቅረባቸው ነው፡፡

የሸማቾች እና የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች የሻወር ውሃ ግፊትን ከዚህ በላይ መጨመር አላስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ለብክነት ይዳርጋል ብለዋል፡፡

ይህ የሻወር ቧንቧ ውሀ ደንብ ሊቀየር የታሰበው የአሜሪካ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለሥልጣን ባለፈው ወር በዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን ቅሬታ ተንተርሶ ነው፡፡

‹‹እነዚህ የሻወር ውሃ ማፍሰሻዎች ግን…›› አሉ ትራምፕ ከሳምንታት በፊት፣ ‹‹…ለመሆኑ ውሃ በበቂ ይፈስላችኋል? ለኔ ግን ውሃ አይወርድልኝም፡፡ ልብስ አውልቃችሁ ለረዥም ሰዓትሻወር ቤት ገብታችሁ ትቆማላችሁ፣ ውሀው ግን ግፊት የለውም፡፡ ስለናንት ባላውቅም እኔ ግን በተለይ ፀጉሬን በደንብ በሚፈስ ውሃ መታጠብ እፈልጋለሁ፡፡››

የአሜሪካ የኃይል ጥበቃና የቁሳቁሶች ደረጃ መዳቢ ቡድን ኃላፊ አንድሩ ዴላስኪ ‹‹ትራምፕ ያቀረቡት ሀሳብ ‹የጅል ሐሳብ›› ብለውታል፡፡

በያንዳንዱ የሻወር ቧንቧ ቀዳዳ 2.5 ጋሎን ውሀ ይፍሰስ ማለት በጠቅላላው በደቂቃ ከ10 እስከ 15 ጋሎን ማለት ነው፡፡ ይህ የውሃ ግፊት ሻወር የሚወስደውን ሰውዬ ከሻወር ቤት ጠርጎ ሊያስወጣው ሁሉ ይችላል ብለዋል ለአሶሺየትድ ፕሬስ።

በትራምፕ ምክንያት የሚቀየረው ደንብ ወደ ፍርድ ቤት ሊሄድ ይችላል ብሏል ሮይተርስ፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ፀጉራቸው ሰው ሰራሽ ነው ወይስ የተፈጥሮ የሚለው አሁንም የመገናኛ ብዙኃንት መነጋገርያ ነው፡፡