ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቻይና ተጠቃሚዎች የሚያዙት የምግብ መጠን ላይ ገደብ ሊበጅ ነው
ቻይና የምግብ ብክነትን ለማስቀረት ቆርጣ እንደተነሳችና በርካታ እርምጃዎችን ለመውሰድ መዘጋጀቷን አስታውቃለች። ፕሬዝዳንት ሺ ዢን ፒንግ በአገሪቱ የሚስተዋለውን የምግብ ብክነት '' አስደንጋጭና አሳዛኝ'' ሲሉ ገልጸውታል።
'ክሊን ፕሌት ካምፔይን' ወይም በአማርኛ ንፁህ የምግብ ሰሀን እንቅስቃሴ የተጀመረው ፐሬዝዳንቱ ከኮቪድ-19 በኋላ የምግብ ብክነት ቁልጭ ብሎ ታይቷል ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም '' የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ ይህንን ጉዳይ ልንከታተለው ይገባል'' ብለዋል።
በተጨማሪም በቻይና ለሳምንታት በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በርካታ የደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች በጎርፍ መመታታቸውን ተከትሎ በቶኖች የሚቆጠር የገበሬዎች ምርት እንዳልንበር ሆኗል።
ነገር ግን የቻይናው ብሄራዊ የዜና ተቋም 'ግሎባል ታይምስ' እነዚህ ምክንያቶች የምግብ እጥረት የሚያስከትሉ አይደሉም ካለ በኋላ የምግብ ብክነት በራሱ ግን እንደ ትልቅ ጉዳይ ሊታይ እንደሚገባው ገልጿል።
የቴሌቪዥን ጣቢያው በበይነ መረብ አማካይነት በርካታ ምግቦችን ሲመገቡ በቀጥታ የሚያስተላልፉ ሰዎች ላይም ወቀሳ መሰል አስተያየት ሰጥቷል።
የሺ ዢን ፒንግን ንግግር ተከትሎም የዉሃን የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሩ ማህበር ምግብ ቤቶች ለተጠቃሚዎች የሚያቀርቡት የምግብ ቁጥር ላይ ገደብ እንዲያስቀምጡ እየወተወተ ነው።
በዚህም መሰረት በቡድን የሚመጡ ሰዎች ካላቸው ቁጥር በአንድ ያነሰ የምግብ አይነት ብቻ ነው ማዘዝ የሚችሉት። አራት ሰዎች ወደ አንድ ምግብ ቤት ጎራ ብለው አራት ምግብ ማዘዝ አይችሉም ማለት ነው።
ስለዚህ አዝዘው መመገብ የሚችሉት ሶስት ምግብ ብቻ ይሆናል።
ነገር ግን ይህ አሰራር ወደ ማህበረሰቡ ዘልቆ እስከሚገባ ብዙ ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል ተገምቷል። በቻይናውያን ባህል መሰረት ደግሞ ከሚመገቡት ምግብ በላይ ማዘዝ እንደ ጥሩ ነገር የሚቆጠር ነው።
ሰዎች በቡድን ሆነው ሲመገቡ ሰሀኖችና ትሪዎች ባዶ ሆነው ከታዩ አስተናጋጁ ግለሰብ ወይም ድርጅት እንደ መጥፎ እንግዳ ተቀባይ ነው የሚቆጠረው።
'ኤን-1' የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ሀሳብ በበርካቶች ትችትን አስተናግዷል። "በጣም አስጨናቂ ነገር ነው" ብለው የተከራከሩም አልጠፉም።
'' አንድ ሰው ብቻውን ወደ ምግብ ቤት ቢሄድስ? ምን ያክል ምግብ ነው ማዘዝ የሚችለው? ምንም?'' ሲል አንድ ግለሰብ በአንድ የቻይና ማህበራዊ ሚዲያ በኩል ሀሳቡን አስፍሯል።
ሌሎች ደግሞ አብዛኛዎቹ ምግብ ቤቶች ምግብ እንዲባክን አያደርጉም፤ እንደውም በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው በየአጋጣሚው ምግብ እንዲባክን የሚያደርጉት ብለዋል።
የቻይናው የዜና ወኪል ሲሲቲቪ በበኩሉ በቀጥታ ስርጭት በአንድ ጊዜ ብዙ ምግብ በአፍ የመጉረስ ትእይንት የሚያሳዩ ግለሰቦችም ለዚህ ብክነት አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሆነ ገልጿል።
''ሙክባንግ' በመባል የሚታወቁት እነዚህ የቀጥታ ስርጭቶች በብዙ የቻይና አካባቢዎችና እስያ አገራት ተወዳጅ ናቸው።
ቻይና ይህን መሰል የምግብ ብክንትን የመከላከል እንቅስቃሴ ስትጀምር ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። በአውሮፓውያኑ 2013 እጅግ የተጋነኑ የምግብ ድግሶችን እና የባለስልጣናት ግብዣዎችን ለማስቀረት ስራዎችን አከናውና ነበር።
አንድ ቻይና ውስጥ የሚንቀሳቀስና አካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰራ ድርጅት እንዳስታወቀው በአውሮፓውያኑ 2015 በአገሪቱ ከ17 እስከ 18 ሚሊዮን ቶን ምግብ ተርፎ ተደፍቷል።