ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሂዩማን ራይትስ ዎች፡ የየመን ታጣቂዎች ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን አባረዋል፤ ገድለዋል
የሁቲ ታጣቂዎች ኮቪድ-19ኝን ምክንያት በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ከሰሜናዊ የመን አስወጥተዋል እንዲሁም ገድለዋል ሲል ሂዩማን ራይተስ ዎች የተሰኘው ተቋም አስታውቋል።
ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ እንደሚያትተው ወደ ሳዑዲ ድንበር የተባረሩት ስደተኞች በድንበሩ ጠባቂዎች ሌላ ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ የተወሰኑ ሰዎች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩት ወደ ተራራማ አካባቢ ሸሽተዋል ይላል።
ድምፃቸውን ለመብት ተሟጋቹ ድርጅት የሰጡ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ለቀናት ያለምግብና ውሃ እንደቆዩ ተናግረው ከዚያ በኋላ ወደ ሳዑዲ መግባት ቢችሉም ንፅሕና በሌለው ሥፍራ ታጉረው እንደከረሙ ተናግረዋል።
ሕፃናትን ጨምሮ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አሁንም በየመንና ሳዑዲ ተራራማ ድንበር አካባቢ ሊኖሩ እንደሚችሉ ድርጅቱ ይገምታል።
የድርጅቱ ጥናት ቡድን አባላት ናዲያ ሃርድማና የሳዑዲና የየመን ኃይሎች ኢትዮጵያዊኑ ላይ የፈፀሙትን ግፍ ወቅሰው የተባበሩት መንግሥታት ለጉዳዩ መፍትሔ እንዲሰጠው አሳስበዋል።
ድርጅቱ ሰኔና ሐምሌ ወር ላይ 19 ኢትዮጵያውያንን ማለትም 13 ወንዶች፣ 4 ሴቶችና ሁለት ታዳጊ ሴቶች አናግሯል።
ከመስከረም 2014 ጀምሮ የየመን ዋና ከተማ ሰንዓን የተቆጣጠሩት የሁቲ አማፅያን በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን አል ጋር የሚባል አካባቢ ከበው ጥቃት እንዳደረሱባቸው ድርጅቱ ያናገራቸው ስደተኞች ያስረዳሉ።
ይህ የሆነው ወርሃ ሚያዚያ ላይ ሲሆን ከዚያም ስደተኞቹን የጭነት መኪና ላይ አሳፍረው ወደ ሳዑዲ ድንበር እንደወሰዷቸውና ሊያመልጡ የሞከሩ ሰዎች ላይ እንደተኮሱ ሂዩማን ራይትስ ዎች አስታውቋል። የድርጅቱ ምንጮች እንደሚሉት ታጣቂዎቹ ስደተኞቹ ኮሮናቫይረስ ሊኖርባቸው ይችላል በሚል ከአል ጋር ያባረሯቸው።
ተቋሙ ያናገራት አንዲት ሴት "ሁለት ሰዎች ሲሞቱ አይቻለሁ" ስትል ሌላ ሴት ደግሞ "ታጣቂዎቹ ሥፍራውን ለቀን እንድንወጣ ሲያዋክቡን ነበር በዚህም መካከል 40 ያክል ሰዎች እንደሞቱ ማየት ችያለሁ" ብላለች።
ለድርጅቱ ቃላቸውን ከሰጡ 19 ሰዎች መካከል 12 ሰዎች፤ ስደተኞች ሲገደሉ የተመለከቱ ቢሆንም የሟቾች ቁጥር በይፋ ምን ያክል እንደሆነ ማወቅ አልተቻለም ይላል መግለጫው።
አል ጋር የተሰኘው ኢ-መደበኛ የስደተኞች ጣቢያ በርካቶች ተጠልለው የሚኖሩበት ነው። ሂዩማን ራይትስ ዎች ጥቃቱ ተፈፅሟል ከተባለት ወቅት በፊት እንዲሁም በኋላ ያሉ የሳተላይት ምስሎችን ተመልክቶ ቢያንስ 300 መጠለያ ሸራዎች ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን ተገንዝቧል።
ስደተኞቹ፤ ከሳዑዲ አረቢያ ድንበር ጠባቂዎች አምልጠው በሥፍራው በሚገኝ አንድ ወንዝ አቅራቢያ ቢደበቁም በወታደሮቹ ተይዘው ወደ 'ወታደራዊ ካምፕ' መወሰዳቸውንና በካምፑ ለሰዓታት መቆየታቸውን ይናገራሉ።
ስምንት ስደተኞች የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች ገንዘብና ሌሎች ንብረቶችን እንደወሰዱባቸውና በቀጣዮቹ ቀናት ደቡባዊ ሳዑዲ ወደ ሚገኝ አል-ጂዛን የተባለ የማጎሪያ ጣብያ እንደወሰዷቸው ተናግረዋል።
የሳላይት ምስሎችን የተጠቀመው ሂዩማን ራይትስ ዎች ስደተኞቹ ታጉረን ነበር ባሏቸው ሥፍራዎች የሚገኙ ካምፖችን መመልከት ችሏል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች አሁን ጂዛን የሚገኙ 6 ኢትዮጵየዊያን ወንዶችና፤ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በለይቶ ማቆያ ያሉ 6 ሴቶችን አናግሮ ሁሉም በጂዛን ጣብያ ታጉረው ለቀናት እንደቆዩ ተናግረዋል።
ስደተኞቹ፤ ማጎሪያ ጣብያው በጣም የተጨናነቀ፣ በቂ መፀዳጃ ክፍሎች የሌሉት፣ አልጋና ብርድ ልብስ የማይገኝበት፣ የሕክምና አገልግሎት የሌለው እንደሆነና ብዙዎቹ ወለል ይተኙ እንደነበር ተናግረዋል። ድርጅቱ ከስደተኞቹ የፎቶና የተንቀሳቃሽ ምስሎች መረጃ እንዳገኘ መግለጫው ላይ አስፍሯል።
ድርጅቱ፤ የሁቲ ኃላፊዎች ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ ግፍ የፈፀሙትን ታጣቂዎች መርምረው እንዲቀጡ ብሏል። አልፎም የሳዑዲ መንግሥት የድንበር ጠባቂዎቹን እንዲመረምርና ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል። ስደተኞቹ የሚገኙባቸው ማጎሪያ ጣብያዎችን ሁኔታ እንዲያሻሽልም ድርጅቱ ለሳዑዲ መንግሥት ማሳሰቢያ አስተላልፏል።
የሳተላይት ምስሎችና ከስደተኞች የተገኙ ምስሎችና ሌሎች ብርካታ መረጃዎች የተካተቱበት ዘርዘር ያለው የድርጅቱ መግለጫ በየመን በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት በርካታ ስደተኞች በሕይትና ሞት መካከል እንዳሉ ያስረዳል።
2019 ላይ የተገኘ አንድ መረጃ እንደሚያሳየው የመንን እንደ ሁለተኛ ሃገር ከሚጠቀሙ ስደተኞች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን ናቸው።