የአሜሪካ ምርጫ፡ ባይደን ወይስ ትራምፕ? ቅድመ ምርጫውን ማን እየመራ ነው?

ከሰዓታት በኋላሬ፤ አሜሪካውያን ቀጣይ መሪያቸውን ይለያሉ።

ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣናቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ? ወይስ ይቀጥላሉ? የሚለው የሚለይበት ቀን።

ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ከዴሞክራቱ ጆ ባይደን ጋር አንገት ለአንገት የተናነቁት ፕሬዝደንት ትራምፕ ቁርጣቸውን የሚያውቁት ከሰዓታት በኋላ ነው።

ባይደን ከ1970ዎቹ ጀምሮ የአሜሪካን ፖለቲካ ቅርጥፍ አድርገው የበሉ ሰው ናቸው። ከትራምፕ አስተዳደር በፊት የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል።

ማን ይረታ ይሆን? ጥቅምት 24 ያገናኘን።

ነገር ግን የአሜሪካ የምርጫ ትንቅንቅ የምርጫ ዕለት ብቻ የሚታይ አይደለም። የቅድመ ምርጫ ምርጫም አለው። ድምፅ ሰብሳቢ ድርጅቶች የትኛውን ዕጩ ነው የምትመርጡት እያሉ ከአሜሪካውያን የሚሰበስቡትን ድምፅ ይፋ የሚያደርጉበት ነው ቅድመ ምርጫ ማለት።

እና በዚህ ቅድመ ምርጫ ማን እየመራ ነው? ትራምፕ ወይስ ባይደን?

የቅድመ ምርጫ ድምፆች የትኛው ዕጩ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ማሳያ ናቸው። ነገር ግን ምርጫውን አሸናፊ ማነው የሚለውን በትክክል ላይገምቱ ይችላሉ።

ለምሳሌ፤ በጎርጎሳውያኑ 2016 ሂላሪ ክሊንተን በቅድመ ምርጫው ትራምፕን አስከንድተው ሲመሯቸው ነበር። ነገር ግን በዋናው ምርጫ መሸነፋቸው አይዘነጋም።

ለነገሩ በዋናውም ምርጫ ቢሆን ሂላሪ ክሊንተን ከትራምፕ በሶስት ሚሊዮን የላቀ ድምፅ ማምጣታቸው አይዘነጋም። ቢሆንም አሜሪካ 'ኢሌክቶራል ኮሌጅ' ሥርዓትን ስለምትጠቀም ብዙ ሰው ድምፅ የሰጠው ዕጩ ያሸንፋል ማለት አይደለም።

በዘንድሮው ቅድመ ምርጫ ድምፅ ጆ ባይደን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን እየመሩ ይገኛሉ። በተሰበሰቡት ድምፆች መሠረት ባይደን ከትራምፕ ቢያንስ በ10 ነጥቦች ልቀው ይገኛሉ።

ዋነኛ የፉክክር ግዛቶች

አሜሪካውያንና ዓለም ከ2016 ምርጫ የተማሩት ነገር ቢኖር ብዙ ድምፅ ማግኘት ማለት ምርጫ ማሸነፍ ማለት አለመሆኑን ነው።

በአሜሪካ ምርጫ ለማሸነፍ ወሳኝ የሚባሉ ግዛቶች አሉ። ፕሬዝደንታዊ ዕጩዎች እነዚህን ግዛቶች ለማሸነፍ የሞት ሽረት ትንቅንቅ ያደርጋሉ።

የአሜሪካ ግዛቶች በአጠቃላይ 538 ድምፆች ተከፋፍለው ይዘዋል። ነገር ግን እኒህ ድምፆች ለ50ዎቹ ግዛቶች እኩል የተከፋፈሉ አይደሉም። የምርጫ አውድማ የሚባሉት እኒህ ግዛቶች ከሌሎች ግዛቶች የበለጠ ድምፅ አላቸው።

እስካሁን ድረስ የተሰበሰቡት ድምፆች እንደሚጠቀሙት ባይደን በሚቺጋን፣ ፔንሲልቫኒያ እና ዊስኮንሲን ግዛቶች የተሻለ ተቀባይነት አላቸው። ትራምፕ ከእነዚህ ግዛቶች በሰበሰቡት ድምፅ ነው በጠባብ ውጤት ያለፈውን ምርጫ መርታት የቻሉት።

ጆ ባይደን፣ በእነዚህ ግዛቶች ብቻ ሳይሆን ባለፈው ምርጫ የትራምፕ ናቸው ተብለው በነበሩት ኦሃዮና ቴክሳስ ግዛቶችም የተሻለ ተቀባይነት አግኝተዋል።

ኮሮናቫይረስና ትራምፕ

ፕሬዝደንት ትራምፕ ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና የሰጡት ምላሽ በብዙዎች ዘንድ እንዲተቹ አድርጓቸዋል።

ትራምፕ መጋቢት ላይ በወረርሽኙ ምክንያት ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ሲደነግጉ ተቀባይነታቸው ጨምሮ ነበር። 55 በመቶ አሜሪካውያን በወቅቱ ድምፃቸውን ለእሳቸው ሊሰጡ እንደሚችሉ አንድ ድምፅ ሰብሳቢ ድርጅት አሳውቆ ነበር።

ነገር ግን በቅርቡ የተሰበሰበ አንድ ድምፅ እንደሚጠቁመው የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች ጭምር ትራምፕን ፊት ነስተዋቸዋል። ለዚህም ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወረርሽኙ ላይ ያላቸውን አቋም እያለሳለሱ ያሉት [ጭምብል መልበስን ጨምሮ] ይላሉ ባለሙያዎች።

ቅድመ ምርጫዎች ለባይደን ያደሉ ይምሰሉ እንጂ ምርጫው ሲቃረብ ነገሮች የተለየ ቅርፅ ሊኖራቸው ይችላል።

ለዚህም ነው ብዙዎች ቅድም ምርጫውን ተውትና ጥቅምት 24 እንገናኝ የሚሉት።