የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ ኢንተርኔት ተቋረጠ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሥልጣን መነሳታችን ተከትሎ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ኢንተርኔት መቋረጡን የኢንተርኔት ነጻነትን የሚከታተለው ኔትብሎክስ አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሊ ካሃይሬን ከፕሬዝዳንቱ ጋር የተጋጩት ምርጫው በሚደረግበት ጊዜ ላይ ባለመስማማታቸው ነው ተብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን መነሳት ተከትሎም በአገር ውስጥና ውጪ ተቃውሞ ተሰምቷል።
የአውሮፓ ሕብረት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ የሆኑት ጆሴፕ ቦረል አሊ ካሃይሬን ከስልጣን ለማንሳት የተወሰደው እርምጃ "ለሕገ መንግሥታዊ መሰረቱ ክብር ማጣት ነው" ብለውታል።
የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትሩ በበኩላቸው "ጨለማው ቀን" ሲሉ ክስተቱን ገልፀውታል።
ኔትብሎክስ አክሎ እንዳስታወቀው ኢንተርኔት ሆን ብሎ መቋረጡንና ከማንኛውም ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ ጋርም መገናኘቱ አለመጠቀሱን ገልጿል።
ካሃሬን ከሥልጣን ለማንሳት የሕዝብ ተወካዮች በሙሉ ደምጽ የወሰኑ ሲሆን፤ ከ178 ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት 170 ዎቹ ደግፈውታል።
ፕሬዝዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ "ፎርማጆ" እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል ቀጣዩን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሚመለከት የሥልጣን ሽኩቻ እንደነበር ተሰምቷል።
ከሥልጣናቸው የተነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫው መካሄድ ያለበት በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት የካቲት ወር እንደሆነ ቢገልጹም፤ ፕሬዝዳንቱ ግን በዚያ መሰረት መሄድ የሚችለው ለአንድ ሰው አንድ ድምጽ በሚለው መርህ መሰረት ከሆነ ነው ሲሉ እንደሚከራከሩ ተገልጿል።
በአሁኑ ሰዓት የሶማሊያ ጎሳዎች ተወካዮቻቸውን የሚመርጡ ሲሆን የሕዝብ ተወካዮቹ ደግሞ ፕሬዝዳንቱን ይመርጣሉ። ጉዳዮን በቅርበት የሚከታተሉ ፕሬዝዳንቱ የሚያቀርቡት ሃሳብ ምርጫውን በተቀመጠለት ጊዜ ለማድረግ ከፍተኛ ሃብት በማስፈለጉና በርካታ መራጮችን መመዝገብ ስለሚጠይቅ እንደማይቻል በማንሳት ይሞግታሉ።
አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እስኪሾም ድረስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማሃዲ ሞሐመድ ጉሌድ ቦታውን ሸፍነው እንዲሰሩ በፕሬዝዳንቱ ተጠይቀዋል።












