በስተርጅና የኢንስታግራም ሞዴል የሆኑት ባልና ሚስት

የፎቶው ባለመብት, Instagram/WantShowAsYoung
በዚህ ዕድሜዬ ሰዎች የእኔን ፎቶ ማየት ይሻሉ ብዬ አስቤ አላውቅም ይላሉ የ84 ዓመቷ ሱ ሂሱ ሂ።
ልክ እንደ ኮረዳ ሞዴሎች ሁሉ እማማ ሱ ሂሱም ፈገግ፣ ሞንደል፣ ወዝወዝ እያሉ ፎቶ ይነሳሉ። ለላውንደሪ ማስታወቂያ የሚሆኑ በደረቁ በታጠቡ ልብሶች አጊጠዋል።
ላለፉት 70 ዓመታት እማማ ሱ እና የ83 ዓመቱ ባለቤታቸው አባባ ዋን ጂ በታይዋን ሀውሊ ክፍለ ከተማ ልብስ ሲያጥቡ ነው የኖሩት። ላውንደሪ ቤት አላቸው።
ብዙ ሰዎች ይታጠብልን ብለው የሰጧቸውን ልብሶች ዘንግተውት ኖረዋል። በቅርቡ የልጅ ልጃቸው ሪፍ ቻንግ ታዲያ አንድ ሐሳብ አቀረበላቸው።
ለምን ሰዎች የረሷቸውን ልብሶች እየለበሳችሁ ፎቶ አትነሱም ይላቸዋል።
"ኧረ ምን በወጣን! አሉ አሮጊቷና ሽማግሌው ባልና ሚስት። ደሞ በስተርጅና እንቅበጥ እንዴ ሳይሉ አልቀሩም።
የልጅ ልጃቸው ግን ወትውቶ፣ ወትውቶ በመጨረሻ አሳመናቸው። አሁን ከመላው ዓለም 130ሺህ ተከታዮችን አፍርተዋል። የኢኒስታግራም ከዋክብት ሆነዋል።
የልጅ ልጃቸው በኋላ ላይ እንደተናገረው ሐሳቡን ሲያመነጭ ዓላማው አያቶቹን ዝነኛ ማድረግ አልነበረም፤ "እኔ ሐሳቡን ያቀረብኩላቸው ከድብታ እንዲያወጣቸው በሚል ነበር። አለ አይደል? እንዲሁ መደበርያ እንዲሆናቸው. . ."

የፎቶው ባለመብት, Instagram/WantShowAsYoung
የልጅ ልጅ ይህን ሐሳብ ሲያመነጭ አያቶቹን ከድብርት ከማውጣትም ባሻገር ልብሶቻቸውን ከላውንደሪው ያልወሰዱ ሰዎች መጥተው እንዲወስዱም ያበረታታቸዋል ብሎም አስቦ ነበር።
ሽማግሌዎቹ ባልና ሚስት ዝናቸው እየተመነደገ ሲሄድ የፋሽን መጽሔቶች እየመጡ ፎቶዎች መውሰድ ጀመሩ። አሮጊቷ በአጭር ቀሚስ ሽማግሌው ደግሞ በቁምጣ ሆነው ልክ ለሽርሽር የሚሄዱ ነው የሚመስሉት።
እንደዚያ ስዘንጥ የ30 ዓመት ጎረምሳ የሆንኩ ያህል ነው የሚሰማኝ ይላሉ ሽማግሌው ዋን ጂ።
አባባ ዋን ጂ የደረቅ እጥበት ላውንደሪ የጀመሩት በ14 ዓመታቸው ነው። ድሮ ሰው ልብሱን አሳጥቦ ላውንደሪ ውስጥ አይረሳም ነበር። አሁን አሁን ግን ልብስ ርካሽ እየሆነ ሲመጣ ሰው ልብሱን ላውንደሪ ይረሳ ጀምሯል ይላሉ።
"አስታውሳለሁ. . . እኔ ሳገባ አንድ ፈረስ ጋሪ ሙሉ ኩንታል ሩዝ ሽጬ ነበር ሱፍ ልብስ የገዛሁት። ልብስ ድሮ ቀረ. . .።"
አባባ ዋን ጂ እንደሚሉት ሰዎች ልብሶቻቸውን የሚረሱት አንድም ሀብታም ስለሆኑ ነው፤ አንዳንዴ ግን የልብሱ ባለቤት ስለሚሞት ነው።
የዋን ጂ እና የባለቤታቸው የዕድሜ ጀምበር ወደ መጥለቂያዋ ተቃርባለች። ነገር ግን የዚህችን ዓለም ኮንትራት ጨርሰው እስኪሄዱ ድረስ እየዘነጡ በኢኒስታግራም ላይ ዓለማቸውን እየቀጩ ይቆያሉ።














