ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አውሮፕላኑ መታጠቢያ ቤት ውስጥ 'ቦምብ አለ' የሚል ማስታወሻ በማግኘቱ የተነሳ በረራውን አቋረጠ
ከክራኮው ደብሊን እየበረረ የነበረው ራይናኤር በአውሮፕላኑ ውስጥ ቦምብ መኖሩን የሚገልጽ ማስታወሻ በንጽህና ቤት ውስጥ በመገኘቱ የተነሳ በረራውን አቋርጦ ለማረፍ ተገደደ።
ራይናኤር በረራውን አቋርጦ ያረፈው ኤሴክስ ስታንስቴድ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ሲሆን ፖሊሶችም አውሮፕላኑን በሚገባ መፈተሻቸው ተገልጿል።
አውሮፕላኑ ሲያርፍ ሁለት የጦር ጄቶች አጅበውት እንደነበር የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ " አውሮፕላኑ በሰላም ነው ያረፈው፥ ነገር ግን መንገደኞች ከመውረዳቸው በፊት ራቅ ያለና ደህንነቱ የተጠበቀ ስፍራ እንዲቆም ተደርጓል" ሲሉ ተናግረዋል።
በትዊተር ላይ አውሮፕላኑ በጦር ጄቶች ታጅቦ ሲያርፍ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ተጋርተዋል።
አውሮፕላኑ ሲያርፍ የተመለከተው ኪርቢ ከኤሲክስ እንዳለው "የአውሮፓ ተዋጊዎች ስታንስቴድ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ እያንዣበቡ ነበር የሚመስለው"
የራይናኤር ቃል አቀባይ በበኩላቸው "አውሮፕላኑና መንገደኞቹ ተፈትሸዋል፤ የዩናይትድ ኪንግደም ፖሊስ ወደ ደብሊን መቼ መብረር እንደሚችሉ ይወስናል" ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
"ደብሊን ወደ ክራኮው ለመሄድ እየጠበቁ የነበሩ መንገደኞች እንዳይዘገዩ በማሰብ ወደ ሌላ አውሮፕላን እንዲሸጋገሩ ተደርጓል"
የኤሴክስ ፖሊስ "ሁሉም መንገደኞች ከአውሮፕላኑ ላይ በሰላም ወርደዋል። አውሮፕላኑም በስታንስቴድ ነጠል ባለ ስፍራ ይቆያል፤ እኛም ምርመራችንን እንቀጥላለን" ብሏል።