ድምጻዊ አሊ ቢራ ስለ ሃጫሉ ሁንዴሳ ምን ይላል?

ሙዚቃን ለትግል በመጠቀም እና ለትግል በማነሳሳት ረገድ ሃጫሉ ሁንዴሳንና አሊ ቢራን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ።

በኦሮምኛ ሙዚቃ አዋቂዎችም ዘንድ ድምጻዊ ሃጫሉ የዚህ ዘመን አሊ ቢራ ነው፤ ለሚቀጥሉት አስርት አመታት ከአሊ ቢራ ተቀብሎ ወደሚቀጥለው ትውልድ የሚያስተላልፍ ነው ሲሉ ይገልጹታል።

እነዚህ ሁለቱ ድምጻውያን ይተዋወቁ ነበር አሊ ቢራስ አርቲስት ሃጫሉን እንዴት ይገልጸዋል?

"ለኔ ሃጫሉ የጀግኖች ጀግና ነው፤ የምንኮራበት ነው።" በማለት አሊ ይናገራል።

መጀመሪያ እነዚህ ሁለት ሰዎች፣ አሊ ቢራና ሃጫሉ፣ የተዋወቁት በአካል አልነበረም። "ኢትዮጵያ ከመምጣቴ በፊት የዛሬ 15 ዓመት አካባቢ የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ ነው ያየሁት" ይላል አሊ ቢራ።

የሙዚቃ ቪዲዮውም ላይ አሊ እንዳው ያኔ ሃጫሉ ገና አፍላ ወጣት ነበር ። ነገር ግን ይላል አሊ፣ "ሙዚቃዎቹና የሙዚቃ ቪዲዮዎቹ ስለባህል፣ ሰለ ማንነት፣ ስለ ቋንቋ ቀልብ በሚገዛ መልኩ" ይሰራ ስለነበር አድናቆትም እንዳደረበት ለቢቢሲ ገልጿል።

"በጣም የሚያድግ ትልቅ የኪነጥበብ ባለሙያ የታየኝ ገና ያኔ ነበር" ይላል አሊ ቢራ።

በወቅቱም አሊ ወደ ኢትዮጵያ የሚመላለስበት ጊዜ ሲሆን ጠቅልሎም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ፣ ድምጻዊ ሃጫሉ በሙዚቃ ስሙ ገንኖ፣ ከኦሮምኛ ተናጋሪ ውጪ ያሉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን የሙዚቃ አድናቂዎች ዘንድ ተወዳጅነት አትርፎ ነበር።

ከዚያም አሊና ሃጫሉ በአካልም ተዋወቀው በደንብ መቀራረብ መጀመራቸውን ይናገራል።

"እርሱም የምገልፀው እንደ ሙዚቀኛ ሳይሆን እንደ ጀግና ነው።" የሚለው አሊ የሃጫሉ ሁንዴሳን ጥንካሬ፣ አቋም፣ በዘፈኖቹ የሚያስተላልፋቸው መልእክቶች፣ ከኦሮሞ ህዝብ ተሻግሮ፣ የተጨቆኑ ሰዎች ባሉበት ሁሉ ሊደመጥ የሚችል መልእክት እንዳለውም ይናገራል።

"የሚዘፍንበት ቋንቋ ነው እንጂ ኦሮምኛ የዘፈኑ መልዕክቶች ዓለም ላይ ላለ ለተጨቆነ ሕዝብ ሁሉ የሚሆን ነው።" ይላል አሊ

ለዚህ ነው "የእኛ ጀግና ብቻ ሳይሆን የአለም ህዝብ ጀግና ነው" ብዬ ነው የማየው ሲል ሃሳቡን አጽንኦት ይሰጠዋል።

ነፍሳችን አንድ ናት

"እኔ አቋሜ እንደ ሃጫሉ ነው" የሚለው ድምጻዊ አሊ ቢራ፣ "ለህዝቤ ያለኝ ተቆርቋርነት እንደ ሃጫሉ ነው" በማለት ሁለቱ በሃሳብ አንድ መሆናቸውን ያስረዳል።

"እርሱንም እዚያ መስመር ላይ አየሁት፤ እኛ የኔና የእርሱ ነፍስ አንድ ናት፤ ሃሳባችንም አንድ ነው። እርሱም በዘፈኖቹ ውስጥ ስሜን አንስቷል፤ ይኼ ማለት የአሊ ቢራ መስመር ላይ ነው ያለሁት፤ እርሱ ያለውን ነው እኔም የምለው እንዳለ አድርጌ ነው የምረዳው።"

በዚህም ምክንያት ሞቱ እጅግ በጣም እንደጎዳው ገልጾ እርሱ ብቻ ሳይሆን፣ አሜሪካውያን፣ ጃፓናውያን፣ ኡጋንዳውያን፣ የድምጻዊ ሃጫሉ ስራዎችን ተተርጉመው ቢሰሙ "ሃዘኑም የእነርሱ ጭምር ይሆን" እንደነበር ይገልጻል።

"ከእጃችን ላይ ነጠቁን፤"በአካል እንጂ የነጠቁን ነፍሱ ከእኛ ነጋር አለች" በማለት ሁሌም በሕዝቡ ልብና መንፈስ እንዲሁም ታሪክ ውስጥ አብሮ እንደሚኖር ይገልጻል።

የሃጫሉን ሞት እንዴት ነው የሰማው

ድማጻዊ አሊ የሃጫሉን ሞት ሌሊት ተደውሎ እንደተነገረው ያስታውሳል። "መናገር ነበር ያቃተኝ፤ ደነገጥሁ፤ ህልም ነው እንጂ ይህ እውነት አይሆንም እያልኩ ነበር፤ ሲቆይ ግን እውነት ሆነ።"

ቀናት በተቆጠሩ ቁጥር ሃዘኑ እየበረታ እንደመጣ በመግለጽም በወቅቱ መናገር እንዳልቻለ፣ እጅግ በጣም እንደተጎዳ ለቢቢሲ ገልጿል።

"ያበረታታንኝ ነገር የሃጫሉ ዓይነቶች ብዙ ሚሊየኖች ይመጣሉ። በዚህም በሚቀጥለውም ትውልድ ይነሳሉ ብለን እናስባለን። ይህ ያበረታታኛል።" ብሎ

ከስራዎቹ ውስጥ የትኛዎቹን ነው የምትወደው ተብሎ በቢሲ የተጠየቀው አሊ፣ ለመመለስ ተቸግሮ ነበር።

"ይህኛው ከዚህኛው ይልጣል ብዬ መመምረጥ ይቸግረኛል። ሃጫሉ አስሬ ዘፈን ቢዘፍን፣ ሶስተኛው ጥሩ ነው፤ አስረኛው እንዲህ ነው ማለት ይቸግረኛል፤ ሁሉም እኩል ዋጋ ነው ያላቸው ለእኔ"

የድምፋዊ ሃጫሉን የሙዚቃ ክህሎትም በማንሳት፣ ግጥሞቹን ራሱ እንደሚጽፍ፣ ዜማ እንደሚሰራ፣ ሰው እንኳ ሰርቶ የሰጠው ቢሆን የህዝቡንና የአድማጩን ስሜት በሚኮረኩር መንገድ የማቅረብ ችሎታ ያለው ትልቅ ተሰጥኦ የነበረው ድምጻዊ እንደነበር ይመሰክራል።

ሃጫሉን በቃላት ለመግለፅ የተቸገረው አሊ "በህይወቴ ያየሁት ይህ ልጅ የፈጣሪ መልዕክተኛ እንደሆነ ነው።" ብሏል።

ፈጣሪ ለእያንዳንዱ ህዝብ አንድ አንድ ሰው ያስነሳል የሚለው አርቲስት አሊ ቢራ፣ ሃጫሉም በእነ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ማህተመ ጋንዲ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ ማልኮም ኤክስ ደረጃ እንደሚያየውም ለቢቢሲ አስረድቷል።

"የሕዝቡን ብሶት፣ ያለምንም ፍርሃት፣ አፈሙዝ ፊት ለፊት ሆኖ፣ ሲናገር የነበረ" እንደሆነ ያብራራል።

አስከትሎም እንዴት መታወስ እንዳለበት ለቢቢሲ ሲገልጽ፣ እርሱ ስራዎቹን ሲሰራ ልታወስ ብሎ አለመስራቱን በመጥቀስ ነው።

ነገር ግን በማለት "መታወስ ደግሞ አለበት። ሃውልቶች ማቆም፣ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶች በእርሱ ስም፣ ማን እንደነበር ስለእርሱ ማስተማር አስፈላጊ ነው" ይላል።

በመጨረሻም "ፈጣሪ ጀግናችንን ነፍሱን በገነት እንዲያኖርልን፤ ለወደፊት ደግሞ እርሱን የሚተካ፣ የሕዝባችንንም ፍላጎት ከዳር የሚያደርስ ጀግና እንዲሰጠን እንለምናለን" ብሏል።