በቡራዩ በጎርፍ አደጋ 9 ሰዎች ሲሞቱ የደረሱበት ያልታወቁ እየተፈለጉ ነው

ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በምትገኘው ቡራዩ አካባቢ ቅዳሜ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ቢያንስ 9 ሰዎች መሞታቸውን እና የደረሱበት ያልታወቁ ሰዎች እየተፈለጉ መሆኑን የከተማው ኮሙኒኬሽን አቶ አብደላ ቲቤሶ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አብደላ ቲቤሶ ገፈርሳ ኖኖ የሚባል ቀበሌ እና ገፈርሳ ጉጄ የሚባሉት ቀበሌዎች ውስጥ ባጋጠመው የጎርፍ አደጋ እስካሁን የ9 ሰዎች አስክሬን መገኘቱንና የደረሱበት ያልታወቁ ሰዎች እየተፈለጉ መሆኑን ገለጸው፤ በንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውቀዋል።

በጎርፍ አደጋው ህይወታቸውን ያጡት አብዛኛዎቹ ሰዎች ለሥራ ከሌላ አካባቢዎች የመጡ ሰዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የሟቾችን አስክሬን ማንነት የመለየት ሥራ ላይ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አብደላ እስካሁን ማንነታቸው የታወቁ ሰዎች አስክሬን ወደ ትውልድ መንደራቸው እየተሸኘ መሆኑን ተናግረዋል።

ኃላፊው እንዳመለከቱት በጎርፍ አደጋው እስካሁን በንብረት ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን ባይታወቅም ነገር ግን ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን መገመት እንደሚቻል ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ግዙፍ ፋብሪካዎች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ ሱቆች፣ የመንግሥት ተቋማት እና ቤተ-እመነቶች ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

"አንድ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና በግቢው ውስጥ የነበረ ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ በጎርፉ ተወስዷል" ያሉት አቶ አብደላ፤ በጎርፉ ምክንያት የወደሙ መኖሪያ ቤቶች በቁጥር እስካሁን ባይለዩም በርካታ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ጎርፉ ሳቢያ በርካታ ቁጥር ያላቸው የቤት እንስሳት የሞቱ ሲሆን "የሞቱ ከብቶች፣ ፍየሎች፣ በጎች እና ፈረሶች አሁንም ሜዳ ላይ እንዳሉ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

አንድ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪም በጎርፍ ተወስዶ ሜዳ ላይ ወድቆ እንደሚገኝም አቶ አብደላ ተናግረዋል።

በአካባቢው ይህን መሰል አደጋ ከዚህ ቀደም ተከስቶ እንደማያውቅ አቶ አብደላ ቲቤሶ ለቢቢሲ ገልፈዋል።