በደቡብ አፍሪካ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አጋቾች ባደረሱት ጥቃት አምስት ሰዎች ተገደሉ

በደቡብ አፍሪካ አንድ ቤተክርስቲያን ላይ አጋቾች ባደረሱት ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ። የጥቃቱ መነሻ የሆነው ከቤተክርስቲያኒቱ አመራር ጋር በተፈጠረ ውዝግብ ነው ተብሏል።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስም ጥቃቱ ደረሰበት በተባለበት ከጆሃንስበርግ ወጣ ብሎ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ህፃናትን ጨምሮ በርካታ ምዕመናንን ከአጋቾች ነፃ ማውጣታቸውን አሳውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ አርባ የሚሆኑ ግለሰቦችንና የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተገልጿል።

አለም አቀፍ ፔንጤቆስጣል በተሰኘው በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምዕመናኑን ያገቱት ግለሰቦች በቤተክርስቲያኒቷ አመራር ላይ ጥያቄ ያነሱ ተገንጣይ ቡድን እንደሆኑ የአይን እማኞች አሳውቀዋል።

የቤተ ክርስቲያኗ መሪ ከአራት አመታት በፊት መሞታቸውን ተከትሎ የግጭት መነሻም ሆኖ ነበር ተሏል።

ከሁለት አመታት በፊትም በምዕመናኑ መካከል የተኩስ ልውውጥ መፈጠሩን ተከትሎ ፖሊስም ተጠርቶ እንደነበር አይኦኤል የተባለው ሚዲያ ዘግቧል።

ከአመት በፊትም እንዲሁ 6.5 ሚሊዮን ዶላር ከቤተክርስቲያኗ መዛግብት ጠፍቷል በሚልም ውዝግብ ተፈጥሮ እንደነበርም እንዲሁ ሶዌታን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።

ቅዳሜ እለት ዘጠኝ ሰአት አካባቢ ነው ሲሆን ጥቃቱ የደረሰው፤

የብሔራዊ ፖሊስ ቃለ አቀባይ ብርጋዲየር ቪሽ ናይዱ እንዳሳወቁት አጋቾቹ የቤተ ክርስቲያኗን ግቢ ለመቆጣጠር እንደመጡ ተናግረዋል።

አራት ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ተገድለው በመኪናቸው ውስጥ የተቃጠሉ ሲሆን አንድ የጥበቃ ሰራተኛም እንዲሁ ለመካለከል ሲሞክር ተገድሏል።

ከሰላሳ በላይ የተለያያዩ ጦር መሳሪያዎችም በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ እንደተያዘም ተገልጿል። ፖሊስ እንዳሳወቀው በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የጆሃንስበርግ ፖሊስና የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ይገኙበታል ተብሏል።

አለም አቀፉ የጴንጤቆስጣል ቤተክርስቲያን ሶስት ሚሊዮን ያህል አባላት አሉት።