ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩስያ ጋዜጠኞቿን የምታድነው ለምንድን ነው?
ኢቫን ሳፍሮኖቭ ወታደራዊ ጉዳዮች የሚዘግብ ጋዜጠኛ ነበር። የሩስያ የደህንነት ተቋም ለቼክ ሪፐብሊክ ሚስጥራዊ መረጃ አቀብለሀል በሚል በቁጥጥር ስር አውሎታል።
ሩስያውያን ጋዜጠኞች የታሰረበት ምክንያት “የማያሳምን” ነው ይላሉ።
ኢቫን ፍርድ ቤት የቀረበው የፊጥኝ ታስሮ፣ አንገቱን አቀርቅሮ ነበር። ሁለት ጭምብል ያደረጉ ጠባቂዎች ኢቫን ቀና እንዳይል ይጫኑት ነበር። መናገር የቻለው “ንጹህ ነኝ” የሚል አረፍተ ነገር ብቻ ነበር። ፍርድ ቤቱ ውስጥ በርካታ ደጋፊዎቹ ተገኝተውም ነነር።
የሩስያ ደህነት ተቋም ጋዜጠኛውን ለመያዝ የተጠቀመው የስለላ መንገድ በመንግሥት በኩል ቢመሰገንም፤ ኢቫን ለቼክ ሪፐብሊክ መረጃ ስለመስጠቱ የሚያሳይ ሰነድ ለሕዝብ ይፋ አለመደረጉ አነጋጋሪ ሆኗል።
በሩስያ አገር በመክዳትና በስለላ ተጠርጥረው የሚታሰሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ኢቫንም ከነዚህ አንዱ ነው ብለው ጓደኞቹ ይሰጋሉ።
“ፑቲን ማንም ምንም ቢያስብ ግድ አይሰጣቸውም”
ለመጨረሻ ጊዜ ሩስያ ውስጥ በአገር መክዳት ጋዜጠኛ የተከሰሰው በጎርጎሳውያኑ 1997 ላይ ነበር።
ያኔ ለፍርድ ከቀረቡ አንዱ የሆነው ግሪጎሪ ፓስኮ፤ “20 ዓመታት ወደኋላ የተመለስኩ መሰለኝ” ይላል።
ግሪጎሪ የወታደራዊ ጉዳየች ዘጋቢ ነበር። የሩስያ የባህር ጦር ጥሰት ስለመፈጸሙ በተደጋጋሚ ይጽፋል። ለጃፓን ሚስጥራዊ መረጃ በመስጠት ተከሶ ነበር። 2001 ላይ የአራት አመት እስራት ተፈርዶበታል።
ፍርዱ በሩስያና ከሩስያ ውጪም ተቃውሞ አስነስቷል። ግሪጎሪም አራት ዓመት ሳይታሰር በድርድር ተፈቷል።
“ከዛ በኋላ ጋዜጠኞችን መንካት ፈርተው ነበር። ያኔ ሩስያ የዓለም አቀፉ መዋቅር አካል ስለነበች ለሌሎች አገሮች አስተያየት ቦታ ይሰጡ ነበር። ቭላድሚር ፑቲን ለ20 ዓመታት ስልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ ግን ስለማንም ሐሳብ ግድ የላቸውም” ይላል።
ፕሬዚዳንቱ ለሁለት ተጨማሪ ዓመታት ለመግዛት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻላቸውንም ግሪጎሪ ያጣቅሳል።
“ምንም ገደብ የለም፤ የፈለጉትን ነገር፣ ባሰኛቸው ሰው ላይ፣ እንዳሻቸው መፈጸም ይችላሉ” ሲል ሁኔታውን ይገልጻል።
መንግሥት ኢቫን የታሰረው ጋዜጠኛ ስለሆነ አይደለም ቢልም፤ ግሪጎሪ ግን አይስማማም። መንግሥት እንዲነኩበት የማይፈልጋቸውን ጉዳዮች በማንሳቱ እንደታሰረ ያምናል።
“ጋዜጠኞች እጃቸውን እንዳያስገቡ ማስጠንቀቂያ ነው” ይላል።
የስለላ ክስ በሩስያ
ሩስያ ክሬሚያን በግዳጅ የግዛቷ አካል ማድረጓን ተከትሎ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላት ግንኙነት ሻክሯል። ይህን ተከትሎም ከ2014 ወዲህ በስለላ ክስ የሚመሰርትባቸው ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።
2013 ላይ ሦስት ሰዎች በአገር መክዳት ተከሰው ነበር። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ 15 ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ከዛ በኋላ ቢያንስ 36 ተመሳሳይ ክሶች የተከፈቱ ሲሆን፤ 14 የውጪ አገር ዜጎችም በስለላ ክስ ተመስርቶባቸዋል።
በየዓመቱ፤ ፑቲን የደህንት ሠራተኞቻቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላዮችና የውጪ አገራት ተላላኪዎችን በማጋለጣቸው ያሞግሷቸዋል። እነዚህ ግለሰቦች ምን እንደሚደረጉ ግን አይገለጽም።
የቀድሞው የኤፍኤስቢ ኃላፊ “አገራችን ውስጥ ያሉ የውጪ አገር ሰላዮች እንዳልቀነሱ የሚያሳይ መረጃ አለን” ብለው ነበር። ባለስልጣኖች አዳዲስ የውጊያ መሣሪያዎችንና ወታደራዊ ቴክኖሎጂን የተመለከተ መረጃ በጥንቃቄ እንዲይዙም አሳስበዋል።
የሚታሰሩት ሰዎች እውን ሰላይ ናቸው?
የጋዜጠኛው ኢቫን ጠበቃ ኢቫን ፓቭሎቭ እንደሚሉት፤ ከ2014 ወዲህ ሩስያ በየአቅጣጫው ካሉ ‘ጠላቶች’ ጋር ውጊያ ውስጥ ነን ትላለች። አገሪቱም በከፍተኛ ሁኔታ ወታደራዊ ሆናለች።
ከዓመታት በፊት ጋዜጠኛውን ግሪጎሪ፣ አሁን ደግሞ ኢቫንን የወከሉት ጠበቃ፤ “በዚህ ጉዳይ ለዓመታት ስሠራ አንድም ሰላይ አጋጥሞኝ አያውቅም” ይላሉ።
“ጠላቶችን መያዝ የኤፍኤስቢ ሥራ ነው። እውነተኛ ጠላት ካጡ መፍጠር ስላለባቸው ያገኙትን አካል ይከሳሉ” ይላሉ ጠበቃው።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በቀላሉ መያዝ የሚቻለው ለመረጃ ቅርብ የሆኑና ከተለያዩ አገራት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች ነው። ከዚህ ቀደም ኢላማ ተደርገው የነበሩት ሳይንቲስቶች ሲሆኑ፤ አሁን ደሞ ጋዜጠኞች ላይ እንዳነጣጠሩም ያክላሉ።
ሚስጥሩ ምንድን ነው?
2012 ላይ አገር መክዳትን የተመለከተው አንቀጽ 275 ከተሻሻለ በኋላ ነገሮች ተባብሰዋል።
የሩስያን ደህነት አደጋ ውስጥ በሚከት ሁኔታ ለውጪ አገራት ወይም ተቋሞች፤ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ወይም ማማከርም ያስከስሳል።
ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዞያ ስቬቶና፤ “ይህ ማለት ማንንም ሰው መያዝ ይችላሉ ማለት ነው፤ በ20 ዓመታት ጋዜጠኛን በአገር መክዳት የከሰሱት ሁለት ጊዜ ነው። ነገር ግን ስለላ እየተካሄደ ነው የሚለው ጥርጣኔ ሁሌም አለ” ትላለች።
ባለፉት ዓመታት የቤት እመቤቶች፣ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችና ብዙ ሳይንቲስቶች እንደታሰሩም ትጠቅሳለች።
“የኤፍኤስቢ እስር ቤት የሆነው ለፎርቶቮ በ ‘ሰላዮች’ እና በ ‘ከሀዲዎች’ ተሞልቷል” ትላለች።
ሩስያ ስለላ እየተካሄደ ነው የሚል ጥርጣሬ አይለቃትም የሚለውን ትችት መንግሥት አይቀበለውም።
ቃል አቀባዩ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “የውጪ ሰላዮች ሩስያን አልተዋትም። የሩስያ የመንግሥት ሠራተኖችና የደህንነት ባለሙያዎች ላይ አነጣጥረው ቀን ከሌት ይሠራሉ” ብለዋል።
አያይዘውም፤ “የሩስያ ሰላዮች የውጪ ሰላዮችን ሙከራ ለማክሸፍ አይታክቱም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጋዜጠኛው ኢቫን በመታሰሩ የተነሳውን ተቃውሞ “ስሜታዊ” ብለውታል።
መሰል ክሶች ሲመሰረቱ፤ “የደህነት ጉዳይ ነው” ስለሚባል ለመገምገም አስቸጋሪ ይሆናል። በጉዳዩ የሚሳተፉ ሰዎች ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ይቆጠባሉ። የፍርድ ሂደቱ የሚካሄደውም በዝግ ይሆናል።
የተከሰሰው ጋዜጠኛ ጠበቆች ራሱ ክሱ ምን ላይ እንደተመረኮዘ እስካሁን አላወቁም።
የቀድሞው የሶቭየት ስለላ ኃላፊ የነበሩትና አሁን ተቃዋሚ ፖለቲከኛ የሆኑት ጌናዲ ገድኮቭ እንደሚሉት፤ እውነተኛ ሰላይ ሲያዝ ማስረጃው ለዓለም ሕዝብ ይፋ ይደረጋል።
“ብዙ ጊዜ ማስረጃው ገንዘብ ነው። አንዳንዴ የመረጃ ማስተላለፊያ ፍላሽም ማስረጃ ሊሆን ይችላል። ኤፍኤስቢ አገልግሎቱን ለሕዝብና ለመንግሥት የሚያሳይበት ፕሮፓጋንዳ ነው” ይላሉ።
ከኢቫን ክስ ጋር በተያያዘ አንዳችም ማስረጃ ይፋ አለመደረጉ ነገሩን አጠራጣሪ እንደሚያደርገውም ፓለቲከኛው ያክላሉ።
መልዕክቱ ምንድን ነው?
የኢቫን ጠበቃ እንደሚሉት ከሆነ ከዓመታት በፊት የሕዝብ ጫና ጋዜጠኛው ግሪጎሪ ነጻ አውጥቶታል። አሁን ግን ነገሮች ተለዋውጠዋል።
ከአንድ በመቶ በታች ጊዜ ብቻ ፍርድ እንደሚቋረጥ በመጥቀስ “አሁን ሁኔታው ይከብደናል” ይላሉ።
ጋዜጠኞች የኢቫንን እስር በመቃወም በኤፍኤስቢ ዋና መሥሪያ ቤት አቅራቢያ ሰልፍ ሲያካሂዱ፤ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑት ታስረዋል።
በአንድ ወቅት ግሪጎሪን በመደገፍ ዘገባ የሠራው ብሔራዊ ጣቢያ፤ አሁን ላይ ስለ ሩስያ ‘ጠላቶች’ ዝርዝር ዘገባ እያቀረበ ይገኛል።
“ፑቲንን የእድሜ ልክ መሪ አድርጎ መምረጥ ትክክል እንደሆነ ለማሳመን የሚደረግ ጥረት ነው። ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከዘላለማዊ ጠላቶቻችን እና ከሰላዮች የሚታደገን ፑቲን ብቻ ነው የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ነው የፈለጉት” ሲል ግሪጎሪ ሁኔታውን ይገልጸዋል።