ሜሪ ትራምፕ የፃፉት መፅሐፍ ስለ ፕሬዝደንት ትራምፕ ምስጢራት አዝሏል እየተባለ ነው

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከዶናልድ ትራምፕ ጀርባ የሚታየው የአባትና እናታቸው ፎቶ በዋይት ሃውስ ቢሯቸው ጠረጴዛ የሚገኝ ነው

የትራምፕ ወንድም ልጅ ሜሪ ትራምፕ የፃፉት መጽሐፍ ፕሬዝደንቱን 'እጅጉን ራስ ወዳድ' ሲል ይገልፃቸዋል። 'የእያንዳንዱ አሜሪካዊ ሕይወት አደጋ ላይ ነው' የሚል አንቀፅም ሰፍሮበታል።

ሜሪ ትራምፕ የዶናልድ ትራምፕ ታላቅ ወንድም ልጅ ናቸው። ከሰሞኑ ስማቸው የመገናኛ ብዙሃን አፍ መሟሻ ሆኗል። ምክንያቱ ደግሞ የትራምፕን ግላዊ ምስጢርን የያዘ መጽሐፍ ሊያስትሙ መሆኑ ነው።

የመጽሐፉ ርዕስ በግርድፉ 'ቤተሰቤ የፈጠረው የዓለማችን አደገኛው ሰው' ይሰኛል። የእንግሊዝኛው ርዕስ፡ Too Much and Never Enough: How My Family Created the World's Most Dangerous Man

የትራምፕ አስተዳደር መጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ውንጀላዎች ስህተት ናቸው ይላል። የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን የመጽሐፉ ቅጅ ደርሷቸዋል።

የትራምፕ ቤተሰብ መጽሐፉ አይታተም ሲል ከሷል።

'እጅግ ራስ ወዳድ'

የ55 ዓመቷ ሜሪ ናቸው አጎታቸው ዶናልድ ትራምፕን 'እጅግ ራስ ወዳድ' ሲሉ የገለጿቸው።

ሜሪ፤ በክሊኒካል ሳይኮሎጂ ዶክትሬት ድግሪ አላቸው። "ትራምፕ ደካማ ብቻ አይደሉም" ይላሉ። "በየደቂቃው ስለሳቸው አንድ ነገር መነገር አለበት። ምክንያቱም የሚያወሩትን ዓይነት ሰው እንዳልሆኑ ውስጣቸው ያውቀዋል።"

ሜሪ፤ ዶናልድ ትራምፕ በአባታቸው ፍሬድ ትልቁ ጥላ ሥር እንዳደጉ ይናገራሉ። የትራምፕ አባት፤ የሜሪ አባትን ይበድሏቸው እንደነበርም ጽፈዋል።

የሜሪ አባት የመጠጥ ሱሰኛ ነበሩ። ሜሪ የ16 ዓመት ታዳጊ ሳሉ ነው አባታቸውን ያጡት።

የትራምፕ ቤተሰብ በሪል እስቴት ብር የናጠጠ ነው። የትራምፕ አባት፤ የሜሪ አባት የቤተሰቡን ብር እንዳይወርሱ የቻሉትን ሁሉ ያደርጉ እንደነበር የሜሪ አዲሱ መጽሐፍ ያትታል።

ትራምፕ ትልቁ የሚወዱት ልጃቸውን በመጠጥ ሱስ ሲነጠቁ የነበራቸው አማራጭ ሃብታቸውን ለዶናልድ ትራምፕ አባት ማውረስ እንደነበር አዲሱ መጽሐፍ ያስነብባል።

ዋይት ሃውስ የዶናልድ ትራምፕ አባት ወንድማቸውን ይበድሉ ነበር የተባለው ሐሰት ነው ሲል ያጣጥላል።

ዶናልድ ትራምፕና አባታቸው ፍሬድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕና አባታቸው ፍሬድ በ1980 ዓመተ ምህረት ኒው ዮርክ ውስጥ የተነሱት ፎቶ

የግብር ጉዳይ

ሜሪ ትራምፕ ኒው ዮርክ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ ግብር የከፈሉበትን መረጃ ያቅርቡ ሲላቸው እንዳቀረቡ ጽፈዋል።

ጋዜጣው በወቅቱ የምርመራ ዘገባ በዶናልድ ትራምፕ ግብር መክፈል አለመክፈል ውዝግብ ዙሪያ ሰርቷል።

ሴትዬዋ ፕሬዝደንት "ትራምፕ ግብር ላለመክፈል ያልሄደበት መንገድ የለም" ሲሉ ይከሳሉ።

'አጭበርባሪ ተማሪ'

ሜሪ፤ አጎቷ ዶናልድ የአገሪቱን ብሔራዊ ፈተና ለሌላ ሰው ከፍለው እንዳስፈተኑ በአዲሱ መጽሐፋቸው ላይ ጽፈዋል። ፈተናው አሜሪካውያን ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት የሚፈተኑት ነው።

ሜሪ እንደሚሉት ዶናልድት ትራምፕ ይህን ያደረጉት ራሳቸው ቢፈተኑ ውጤታቸው ለዩኒቨርሲቲ ላያበቃቸው ስለሚችል ነው።

በምትኩ 'ትምህርት የዘለቀው ሌላ ልጅ ቀጥረው ፈተናውን በእሳቸው ስም እንዲፈተን እንዳደረጉ' ይናገራሉ።

"ዶናልድ እንደሆኑ ኪሳቸው ሁሌም ሙሉ ነው። ለተፈተነላቸው ልጅ ጫን ያለ ገንዘብ ነው የከፈሉት።"

ዶናልድ ትራምፕ ኒው ዮርክ የሚገኘው ፎርድሃም ዩኒቨርሲቲ ገብተው ትምህርታቸው መከታተል ከጀመሩ ከቆይታ በኋላ ወደ ፔንሲልቪኒያ ዩኒቨርሲቲ ተዛውረው ነው ዲፕሎማቸውን የጫኑት።

ዋይት ሐውስ፤ ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት አጭበርብረዋል የተባለው ሐሰት ነው ሲል ያጣጥላል።

'ከሴቶች ጋር ያለ ግንኙት'

ሜሪ፤ "ዶናልድ ትራምፕ the Art of the Comeback [ግርድፍ ትርጉም፡ አፈር ልሶ የመነሳት ጥበብ] የተሰኘ መጽሐፍ እንድጽፍለት ጠይቆኝ ነበር" ይላሉ።

ለመጽሐፉ እንዲሆን የሰጧቸው ሃተታ ላይ ዶናልት ሊተኟቸው የሚፈልጓቸው ነገር ግን ፊት የነሷቸው ሴቶችን በሚያንቋሽሽ ቋንቋ የተፃፈ እንደሆነ ሜሪ አዲሱ መፅሐፋቸው ላይ አስፍረዋል።

አልፎም ሜሪ የ29 ዓመት ወጣት ሳሉ ስለተክለ ሰውነታቸው ተገቢ ያልሆነ አስተያየት ይሰጧቸው እንደነበርም ጽፈዋል። በወቅቱ ዶናልድ ትራምፕ ከሁለተኛ ሚስታቸው ማርላ ማፕልስ ጋር ነበሩ።

ትራምፕ ለቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ 'ሜሪ የዕፅ ሱሰኛ ናት፤ በዚህ ምክንያትም ነው ትምህርቷን ያቋረጠችው' ብለው ነግረዋታል ይላል በቅርቡ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው መጽሐፍ። ሜሪ፤ "እርግጥ ነው ትምህርቴን አቋርጬ ነበር ነገር ግን በዕፅ ምክንያት አይደለም" ይላሉ።

ግራጫ መስመር

ሜሪ ትራምፕ አጎታቸው ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ከአደባባይ ርቀዋል። ነገር ግን ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝደንት ከመሆናቸው በፊት ጀምሮ አጥብቀው ይተቿቸው እንደነበር ይታወቃል።

ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ እንደዘገበው ሜሪ፤ ትራምፕ ምርጫ ያሸነፉበትን ምሽት "በሕይወቴ መጥፎው ምሽት" ሲሉ ገልፀውታል።

በወቅቱ ትዊተር ገፃቸው ላይ "ለእናት አገሬ ሃዘን አድርሳለሁ" ሲሉ ፅፈው ነበር።