ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎችን እንዲቀንሱ ለባለስልጣናቱ መልዕክት አስተላለፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት የወጣውን የቤት መቀመጥ መመሪያ ከተጣለ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የምረጡኝ ቅስቀሳ ያደረጉት ስብሰባ ላይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከጠበቁት በታች ሕዝብ መገኘቱ ተነገረ።
በቱልሳ፣ ኦክላሃማ በተካሄደው የዳግም ምረጡኝ ቅስቀሳ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኮሮናቫይረስ ምርመራን አስመልክቶ አወዛጋቢ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ ባለስልጣናት ምርመራዎችን ከማካሄድ ገታ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ብዙ ምርመራ በተደረገ ቁጥር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ "ምርመራ ማለት በሁለት በኩል ስለት ያለው ቢላ ማለት ነው። መጥፎው ነገር ይህ ነው። ብዙ ሰዎች ሲመረመሩ በቫይረሱ የተያዙ ብዙዎችን ታገኛላችሁ። ምርመራውን ገታ አድርጉ በተደጋጋሚ ብልም አሁንም በፍጥነት በመመርመር ላይ ናቸው" ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ አንድ የዋይት ሐውስ ባለስልጣን ፕሬዚዳንቱ እየቀለዱ ነው በማለት ለማስተባበል ሞክረዋል።
ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪ በነጭ ፖሊስ በግፍ በተገደለው ጆርጅ ፍሎይድ ሞት ማግሥት በተከሰተው ተቃውሞ የሚገረሰሱ ሐውልቶችን በተመለከተም "ታሪካችንን ሊያበላሹ የቋመጡ" ናቸው በማለት በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ድርጊቱን አውግዘዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለሁለት ሰዓታት ያህል በተለያዩ ርዕሶች ላይ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በቦታው የተገኘውንም ሕዝብ "ታጋዮች" በማለት አሞካሽተው ደጋፊዎቻቸውን እንዳይገኙ ያደረጉት ሚዲያዎችንም ወንጅለዋል።
ከስብሰባው ስፍራ ውጪ አንዳንድ ረብሻዎች እንደተከሰቱ ሪፖርት ቢደረግም ይህን ያህል የከፋ አልነበረም ተብሏል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በኦክላሃማ ቱልሳ ለሚደረገው ዝግጅትም ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ቲኬት ጠይቀዋልም ብለው ሲኩራሩ ፕሬዚዳንቱ ተሰምተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ነገር ግን አስራ ዘጠኝ ሺህ መቀመጫ ያለውን ማዕከልንም መሙላት አልተቻለም። የተሳታፊው ሕዝብ ቁጥር ከተጠበቀው በታች ለምን እንደቀነሰ ግን የተሰጠ ምክንያት የለም።
በወረርሽኙ ወቅት እንዲህ አይነት የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ ማካሄድ ስጋት አለውም ተብሎ ነበር።
በቅስቀሳው ላይ የተሳተፉ የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎችም ለሽታው ቢጋለጡ የቅስቀሳው አዘጋጆችን ተጠያቂ ላለማድረግ ፈርመው ነው የተሳተፉት ተብሏል።
ቅስቀሳው ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት የምረጡኝ ዘመቻውን ከሚያስተባብሩት መካከል ስድስቱ በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡ ተገልጿል።
የትራምፕ ዳግም ምረጡኝ ቅስቀሳ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በአገሪቱ ብዙ ሕዝብ በአንድ ቦታ የተሰባሰበት ትልቁ ዝግጅት ነው ተብሏል። ዝግጅቱ በተካሄደበት ኦክላሃማ ግዛትም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል።
በአሜሪካ 2.2 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 119 ሺህ ሰዎችም በወረርሽኙ ሰበብ እንደሞቱ ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።












