በጃፓን የእንክብካቤ ማዕከል በጎርፍ ተጥለቅልቆ 14 ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

የሞላውን ወንዝ የሚመለከት ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በጃፓን ደቡባዊ ደሴት ክዩሹ በጣለ ከፍተኛ ዝናብ ሳቢያ በተፈጠረ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ 16 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች የደረሱበት አለመታወቁ ተገለፀ።

ከሟቾቹ 14ቱ የተገኙት በጎርፍ በተጥለቀለቀ አንድ የእንክብካቤ ማዕከል ውስጥ ነው። የሟቾች ቁጥርም ሊጨምር እንደሚችል ተሰግቷል።

ኩማሞቶ እና ካጎሺማ በአደጋው ክፉኛ የተጠቁ ግዛቶች ናቸው።

የኩማሞቶ ገዢ ኢኮ ካባሺማ በእንክብካቤ ማዕከላት የነበሩት ተጎጂዎች ከልብ ህመም ጋር በተያያዘ መሞታቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ የጤና ባለሙያዎች የሞት ምስክር ወረቀት አለመስጠታቸውም ተገልጿል።

አደጋውን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፤ ቤቶችና መኪኖች በጎርፍ ተውጠው ከሚያሳይ ፎቶ ጋር በኩማ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ በጎርፍ ሲወሰድ ያሳያሉ።

ባለሥልጣናትም ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ያዘዙ ሲሆን፤ የነፍስ አድን ሰራተኞችን ለማገዝም 10 ሺህ ወታደሮችን ወደ ሥፍራው ልከዋል።

ይሄው እየጣለ ያለው ዝናብ ዛሬም እንደሚቀጥል ትንበያ ተቀምጧል።

ጠቅላይ ሚኒስተር ሽንዞ አቤ በበኩላቸው ሰዎች በተጠንቀቅ እንዲጠባበቁ አሳስበዋል።

የጃፓን የሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ በአካባቢው እንደዚህ ዓይነት ዝናብ ከዚህ በፊት አጋጥሞ እንደማያውቅ ተናግረዋል።

በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የሚገኙ አንድ ሴት ዝናብ ይህን ያህል ኃይለኛ ሊሆን ይችላል ብለው በእውናቸውም በህልማቸውም አስበው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

ሌላኛዋም በበኩላቸው በአቅራቢ ያለው ወንዝ እየነጎደ ሲወርድ ምን ያህል አደገኛ እንደነበር መረዳታቸውን ገልፀዋል።

የጃፓን ብሔራዊ መገናኛ ብዙሃን (ኤንኤችኬ) ታኪኖ አካባቢ ስምንት ቤቶች በጎርፍ እንደተወሰዱ የሚያስረዱ ዘገባዎች መኖራቸውን ገልጿል።