''ሕይወታችሁን እንደሚወስን አስባችሁ ምረጡ'' ቢዮንሴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታዋቂዋ አቀንቃኝ ቢዮንሴ በቢኢቲ ሽልማት ላይ ላከናወነችው ሰብአዊ ተግባር ምስጋና ስትቀበል ባደረገችው ንግግር ጥቁር አሜሪካውያን በመጪው ምርጫ በንቃት እንዲሳተፉ አሳስባለች።
ያገኘችውን ሽልማት በመላ አገሪቱ በተቃውሞ ላይ ለተሳተፉ ሰዎች ማስታወሻ ይሁንልኝ ያለችው ቢዮንሴ ''የቀደምት አባቶቻችን ትግል መና እንዳልቀረ አሳይታችኋል'' ብላለች።
''እርምጃ እንድተወስዱ አበረታታችኋላው፤ በዘረኝነትና በመድሎ የተሸበበውን ሥርዓት እንድትቀይሩና እንድትታገሉ አሳስባችኋለው።''
''ሕይወታችንን እንደሚወስን ነገር አስበን ልንመርጥ ይገባል፤ ምክንያቱም ብዙ ነገር ይቀይራል'' ብላለች።
ቢዮንሴ ሽልማቷን ከቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ የተቀበለች ሲሆን ለጥቁር አሜሪካውያን ላሳየችው ድጋፍና ቁርጠኝነት ምስጋና ቀርቦላታል።
''በምታደርገው ነገር በሙሉ መመልከት ይቻላል፤ ሙዚቃዎቿ ለጥቁሮች ደስታና ሀዘን ድምጽ ነው፤ ለጥቁሮች ፍትህ እንዲሰጥም ትጠይቃለች'' ብላለች ሚሼል ኦባማ።
በማከልም ''በምትሰሪው ነገር በሙሉ ለተሻለ ነገር እንድሰራ ታነሳሻኛለሽ፤ ሁላችንንም ታነሳሽናለሽ'' ብላለች።
የቢኢቲ ሽልማት ጥቁር አርቲስቶችንና ስፖርተኞችን የሚሸልም ዝግጅት ነው። ከዚህ በፊት በሰብአዊ ተግባር ሽልማት ካገኙ ጥቁር አሜሪካውያን መካከል ታዋቂው ቦክሰኛ ሞሀመድ አሊ፣ የሙዚቃ ፕሮዲዩሰሩ ኩዊንሲ ጆንስ እና የሲቪል መብት መሪው ሬቨረንድ አል ሻርተን ይጠቀሳሉ።
የጆርጅ ፍሎይድና ብሪዮና ቴይለር ሞት እንዲሁም ሌሎች የብላክ ላይቭስ ማተር ተቃውሞ ጉዳዮች በዘንድሮው ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ በሙሉ ተንጸባርቀዋል።የጆርጅ ፍሎይድን የመጨረሻ ደቂቃዎች በሙዚቃ መልክ ያቀረበው ዳቤቢ በምርጥ ወንድ ሂፕ ሆፕ አርቲስት ዘርፍ አሸናፊ መሆን ችሏል።
ሙዚቃውን በመድረክ ሲያቀርብም በመንገድ ላይ ወጥተው ተቃውሟቸውን የሚገልጹ ሰዎች ምስል ከጀርባ የታየ ሲሆን ዳንሰኞችም ''የጥቁሮች ሕይወት ዋጋ አላት'' የሚል መልዕክት ይዘው ታይተዋል።
ጥቁር አሜሪካዊ በመሆኑ ትልቅ ስጋት እንዳለበት በሚገልጽበት ተንቀሳቃሽ ምስል ታዋቂነትን ማትረፍ የቻለው የ12 ዓመቱ ኪድሮን ብራይንት ዝግጅቱን ከፍቶታል።
የዘንድሮው ቢኢቲ ሽልማት በኮሮረናቫይረስ ምክንያት በበይነ መረብ አማካይነት የተካሄደ ሲሆን ንግግሮቹና ዝግጅቶቹ ቀድመው የተቀረጹ ነበሩ።
ታዋቂው ራፐር ሊል ዌይን ከወራት በፊት በሄሊኮፕተር አደጋ ሕይወቱ ላለፈችው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ኮቢ ብራያንት መታሰቢያውን አሰምቷል።
የጅምናስቲክ ተወዳዳሪዋ ሲሞን ቢይልስ ደግሞ በዓመቱ ምርጥ ስፖርተኛ ዘርፍ 12 ጊዜ ማሸነፍ የቻለችው ሴሬና ዊሊያምስን በማሸነፍ የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኛ ተብላለች።
ሜጋን ዚ ስታሊዮን በምርጥ ሴት ሂፕ ሆፕ አርቲስት ዘርፍ አሸናፊ ስትሆን ክሪስ ብራውን ደግሞ በምርጥ ወንድ አር ኤንድ ቢ ዘርፍ ለአምስተኛ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል።












