ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የሙከራ በረራ ሊያደርግ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላን በዚህ ሳምንት ወሳኝ የፍተሻ በረራ ያደርጋል።
ምናልባትም ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆየው የማክስ 737 የበረራ ሙከራ የፋይናንስና የመልካም ስም እጦት ለገጠመው ቦይንግ አንድ እመርታ ተደርጎ ተወስዷል።
ሆኖም የዚህ የሙከራ በረራ ስኬታማነት ማክስ 737 ወደ ገበያ የመመለስ ዋስትናን አይሰጠውም። አውሮፕላኑ ወደ ገበያ ለመመለስ ገና በርካታ ሌሎች ፈተናዎችን ማለፍ ይጠበቅበታል።
በቦይንግ ታሪክ ከፍተኛ ገበያ የነበረው ይህ የአውሮፕላን ሞዴል ሁለት ተከታታይ አደጋዎች ከደረሱበትና ተሳፋሪዎችም ከሞቱ በኋላ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባቱ ይታወሳል።
በኢንዶኒዢያና በኢትዮጵያ አየር መንገዶች አውሮፕላኖች ላይ የደረሱ አደጋዎችን ተከትሎ የዚህ የማክስ 737 አውሮፕላን ግዢን የፈጸሙ፣ አውሮፕላኑን ሲጠቀሙ የነበሩ፣ አውሮፕላኑን ለመረከብ ሲጠባበቁ የነበሩና አዲስ ግዥ ለማድረግ ቀብድ የከፈሉ ጭምር ምርቱ ላይ ጥያቄ በማንሳታቸው ቦይንግ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚደረጉ በበራዎች ስኬታማ ቢሆኑ እንኳ ማክስ 737 ወደ ሰማይ ለመመለስ ገና በርካታ የደኅንነትና የምህድስና ፍተሻዎችን ማድረግ ይጠበቅበታል።
ይህም ሂደት ከዚህ በኋላ በርካታ ወራትን ሊወስድ ይችላል ተብሏል።
የአቪየሽን ተቆጣጣሪዎች ማክስ 737 ቦይንግ አውሮፕላንን ከበረራ ያገዱት የዛሬ 15 ወር ገደማ ሲሆን ይህም የላየን እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ላይ በአምስት ወራት ልዩነት የደረሰውን እጅግ አሰቃቂ አደጋን ተከትሎ ነበር።
በሁለቱ አደጋዎች በድምሩ 346 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የበረራ እግዱን ተከትሎ የ103 ዓመቱ አንጋፋው የቦይንግ ኩባንያ ላይ የካሳና የደኅንነት ጥያቄዎች አንዲነሱበት አድርጓል።
በዚህም ሳቢያ ኩባንያው የከፋ ችግር ውስጥ ገብቶ እንደቆየ ይታወሳል።
በተለይም የአሜሪካ የፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር የአውሮፕላኖችን የበረራ ደኅንነት የሚፈትሽበት መንገድ ላይ በአጠቃላይ ጥያቄ እንዲነሳ ማድረጉ አይዘነጋም።
ቦይንግ መጀመርያ አካባቢ የአደጋዎቹን ችግሮች ከራሱ ለማራቅ ከፍተኛ ሙከራ ሲያደርግ ቆይቶ ነበር።
አደጋውን ተከትሎ የተደረጉ ጥብቅ ምርመራዎች ግን የማክስ 737 አውሮፕላኖች ስሪት ላይ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓታቸው አንዳች ግድፈት እንዳለበት የጠቆሙ ነበሩ።
አሁን ማክስ 737 እነዚህ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓቶቹ ላይ ያደረገውን የምህንድስና ማሻሻያ ተከትሎ ማሻሻያው ምን ያህል ስኬታማ እንደሆነ ለማረጋገጥ መለስተኛ የበረራ ሙከራዎችን በዚያው በቦይንግ ማምረቻ ሲያትል አካባቢ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በዚህ የሙከራ በረራ አብራሪዎች ሆን ብለው የማክስ 737 ግድፈት ነበረበት የተባለውን የኤምካስ ሶፍትዌር ቁልፍን በመጫን አውሮፕላኑ ራሱን በራሱ መቆጣጠር ይችል እንደሆን ይመለከታሉ ተብሏል።
የአሜሪካ የበረራ ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ለአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በላከው ደብዳቤ ዛሬ ለሚጀመረው የሙከራ በረራው ይሁንታ መስጠቱን አስታውቋል።
በዚህ ደብዳቤ ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ እንደገለጸው የማክስ አውሮፕላኖች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ገና ፈቃድ አልሰጠም። ይህ እንዲሆን ገና ብዙ የሙከራ ሂደቶች መታለፍ አለባቸው ብሏል።
ይህ የሙከራ በረራ ይካሄዳል ተብሎ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ባለፈው ዓመት ሲሆን በመሀሉ በአውሮፕላኑ ላይ አንዳች ሌላ ያልተጠበቀ ግድፈት በመገኘቱ ነበር በድጋሚ ሙከራው እንዲዘገይ የተደረገው።
ይህ የሙከራ መለስተኛ በረራ ከተደረገ በኋላ በበራው ሂደት የተገኙ ቴክኒካዊ ነጥቦች አንድ በአንድ ይተነተናሉ፣ ይጠናሉ ተብሏል።
ሙከራው እንከን አልባ ሆኖ ቢጠናቀቅ እንኳ ይህ አውሮፕላን በቀጥታ ወደ ሥራ ይመለሳል ማለት አይደለም።
አብራሪዎችን ከአውሮፕላኑ ጋር እንዲዋሀዱ ለማድረግ የስልጠና መርሀ ግብር ይዘረጋል፣ የአውሮፓና የካናዳ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ደግሞ ለዚህ አውሮፕላን እውቅናና ይሁንታ መስጠት ይኖርባቸዋል።
የአውሮፓ አቪየሽን ኤጀንሲ እንዳስታወቀው ማክስ 737 ከአሜሪካ የአቪየሽን አስተዳደር የጤናማነት እውቅና ተሰጥቶት ወደ ሥራ መመለስ ይችላል የሚል ሰርተፍኬት ቢሰጠው እንኳ ይህ አውሮፕላን በአውሮፓ ሰማይ ላይ ለመብረር ያስችለዋል ማለት አይደለም ብሏል።
ከአውሮፓ የኖርዌይ አየር መንገድ፣ ቲዩአይ እና አይስላንድ አየር መንገድ ይህን የቦይንግ ምርት የሆነውን ማክስ 737 አውሮፕላን ይጠቀሙ የነበሩ ሲሆን ሌሎች አገሮች ደግሞ አውሮፕላኑ እንዲመረትላቸው አዘው ሲጠባበቁ የነበሩ ናቸው።
















