ኢቲ 302 ቦይንግ 737፡ ልክ የዛሬ አንድ ዓመት በኢትዮጵያው አውሮፕላን ላይ ምን ተከሰተ?

ቦይንግ 737 ማክስ 8

የፎቶው ባለመብት, JONATHAN DRUION

ዕሑድ መጋቢት 1 ቀን፣ 2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያዊያን አስደንጋጭ ዕለት ነበር።

እርግጥ 'የኢትዮጵያ'' ታሪኩ የከፍታ ነው። የአቪየሽን ኢንዱስትሪው ሲንደፋደፍ 'ET' ከፍ ብሎ በሯል፤ያውም ለዘመናት።

በትርፍም፣ በአውሮፕላን ብዛትም፣ በበረራ ስፋትም፣ በመስተንግዶ ጥራትም ሞገስ ተለይቶት አያውቅም። በጥቅሉ ከፍ እንጂ ዝቅ ብሎ አያውቅም።

በዚያች ሰንበት ግን 'ማክስ-8' ጎንበስ ካለበት ቀና አልል አለ። አብራሪዎቹ የቻሉትን ሞከሩ። አልሆነም።

የአውሮፕላኑ ሠሪዎች ጥፋቱን በአብራሪዎች ለመደፍደፍ የቀደማቸው አልነበረም። መጀመርያ ጥርጣሪያቸውን አስቀደሙ፤ ቀጥለው የሚዲያ ዘመቻ ከፈቱ።

ችግሩ ከአብራሪዎቹ ካልሆነ ከአውሮፕላኑ ፈጣሪዎች እንደሚሆን አላጡትም። ጣት ወደነርሱ ሲቀሰር ደግሞ ሌላ ቁስል ይቀሰቅሳል፤ ኢንዶኒዢያ። ያን ቁስል መልሶ መነካካት የቦይንግን ስምና ዝና ጠራርጎ የሚወስድ ችግር ያስከትላል። ስለዚህ በቻሉት ሁሉ ነገሩን ከነገርሱ ማራቅ ነበረባቸው።

ያን ዕለት ማለዳ ምን ሆነ?

ከራሱ አልፎ ለአህጉሪቱ አየር መንገዶች በክፉ ጊዜ ደርሶላቸዋል። በዚህ ከፍታ ላይ እያለ ነበር ክፉው አጋጣሚ የተከሰተው።

በማለዳ ዘመናዊውን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ወደ ናይሮቢ አሰማራ።

ብዙ ጊዜ ሙሉ በሚባል ደረጃ ተጓዦችን የሚያስተናግደው የናይሮቢው በረራ 149 መንገደኞችን አሳፍሮ ነበር። ተጨማሪ 8 የአውሮፕላኑ ሠራተኞችም ነበሩበት።

የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ወደ ናይሮቢ ኬንያ ለመብረር እንዲያኮበኩብ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን መልካም ፈቃድ ያገኘው ከጠዋት 02 ሠዓት ከ37 ደቂቃ ነበር።

አውሮፕላኑ ክንፉን ዘርግቶ ተንደርድሮ ተነሳ።

ልክ ከአንድ ደቂቃና ከ10 ሰከንዶች በኋላ ከተለመደው የተለየ ሁኔታ እንዳጋጠመ በአብራሪዎቹ ታወቀ። ረዳት አብራሪው ለዋና አብራሪው ይህንኑ አሳወቀ። ዋና አብራሪውም ችግሩን ለማስወገድ በማለት አውሮፕላኑ በራሱ ሥርዓት እንዲበር ጥረት ማድረግ ጀመረ።

አብራሪዎቹ የገጠማቸውን ችግር ለማስተካከል ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም እንዳሰቡት ሊሳካላቸው አልቻለም። ወዲያውኑ ረዳት አብራሪው ስላጋጠማቸው ነገር ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ሪፖርት አደረገ።

ረዳት አብራሪው ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አውሮፕላኑን የመቆጣጠር ችግር እንደገጠመው አሳወቁ።

ብዙም ሳይቆዩ አውሮፕላኑ ከአብራሪዎቹ ቁጥጥር ውጪ እየሆነ መጣ። አፍንጫውን ወደ ምድር እያገደለ አስቸገረ። አብራሪዎቹ ይህንን ለማስተካከል በከፍተኛ ጥድፊያ ጥረት እያደረጉ ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር በመገናኘት 14ሺህ ጫማ ላይ መቆየት እንደሚሹ ገለጹ።

አውሮፕላኑ ቀና ሊል አልቻለም። ጭራሽ አልታዘዝ አለ። የጀመሩት በረራ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ስላጋጠመው ወደ ተነሱበት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መመለስ እንደሚፈልጉ አሳወቁ። ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ወዲያውኑ ፍቃድ አገኙ። ይህ ሁሉ የሆነው በደቂቃዎች ልዩነት ነበር።

አሁንም አብራሪዎቹ አውሮፕላኑ ካዘቀዘቀበት ከፍ ለማድረግ ጥረታቸው አልተቋረጠም፤ አውሮፕላኑ ግን በስሪቱ ግድፈት እንደሆነ በሚገመት መልኩ አሻገረኝ አለ። ይባስ ብሎ ቁልቁል መምዘገዘግ ጀመረ። በመጨረሻም አብራሪዎቹ ከበረራ ተቆጣጣሪዎች ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ።

የአቶ ተወልደ ትዝታ

ከ150 በላይ ሰዎችን የያዘው የኢቲ302 የአውሮፕላን ሳይከሰከስ እንዳልቀረ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ስጋት ቢገባቸውም ለደቂቃዎች ተስፋ አልቆረጡም ነበረ። ከደቂቃዎች በኋላም የአሰቃቂው አደጋ መከሰት የማይሸሹት እውነት ሆነ።

የአደጋውን መከሰት ቀድመው የሰሙት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሰንበት ቅዳሴን እየታደሙ ነበር።

"የአደጋውን መድረስ ዜና የሰማሁት ጧት ነው። በእርግጥም በጣም ክው አድርጎኛል። በጣም፤ እጅግ በጣም ነው ያሳዘንኩት" ሲሉ መጋቢት አንድ ቀን ጠዋት የተፈጠረባቸውን ስሜት ያስታውሳሉ።

እሁድ ረፋድ ላይ የአደጋውን መከሰት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጽህፈት ቤት በማኅበራዊ ገጹ ላይ አረዳ። በደረሰው አደጋም ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ሁሉ በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ስም ሐዘኑን ገለጸ።

ከዚህ በኋላ አደጋው የዓለም መገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ርእስ ሆነ፤ የአቪየሽን ኢንዱስትሪው ብርክ ያዘው። ተመሳሳይ አውሮፕላን የገዛ ሐሳብ ገባው። ሊገዛ ያሰበ ቀብዴን መልሱልኝ ማለት ጀመረ። የቦይንግ ገበያ ምስቅልቅል ውስጥ ገባ።

በተለይ ከዚህ አደጋ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ የኢንዶኔዢያ ላየን ኤር አየር መንገድ አሰቃቂና በባህሪው ተመሳሳይ አደጋ አጋጥሞት እንደነበር ሲታወስ ነገሮች ወዴት እያመሩ እንደሆነ ግልጽ ነበር።

ለአደጋው ምክንያት ተለያዩ መላ ምቶች ቢቀርቡም በአውሮፕላኑ ላይ ያለ ችግር ሊሆን እንደሚችል በመገለጹ ጥያቄዎች በአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ላይ በረታ።

ይህንንም ተከትሎ ሌላ አደጋን ለማስቀረት እጅግ ዘመናዊ እንደሆኑ የተነገረላቸው ቦይንግ 737 ማክስ 8 ስሪት አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ የማድረግ እርምጃን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ አየር መንገዶች ወሰዱ።

በኢትዮጵያ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ እጅግ የከፋ ስለነበረ አንድም ሰው ከአደጋው አልተረፈም።

ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎ ሜትሮች አካባቢ ርቀት ላይ ከምትገኘው ቱሉ ፈራ ሜዳ ላይ የወደቀውን የአውሮፕላኑን ስብርባሪና የአደጋውን ሰለባዎች አካል ለማግኘት የቀናት ቁፋሮ አስፈልጎ ነበር። ለሟች ቤተሰቦች ሐዘኑ ድርብ ሆነ።

ከአደጋው ጋር በተያያዘ አንዳንድ ወገኖች የአብራሪዎች ችግር አድርገው ለማቅረብ ቢሞክሩም የአደጋው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ግን አብራሪዎቹ ክስተቱን ለማስቀረት መጣራቸውንና በአውሮፕላኑ ላይ የተገጠመው የመቆጣጠሪያ ሥርዓት ለአደጋው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አመልክቶ ነበር።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ተወልደ ገብረማሪያምም ከመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ጋር በተያያዘ "ፓይለቶቹ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሚጠበቅባቸውን ተገቢ እርምጃ በመውሰድ ያላቸውን ከፍ ያለ ሙያዊ ብቃት በማስመስከራቸው" አየር መንገዱ እንደሚኮራባቸው መስክረዋል።

አደጋው በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ሕይወት ከማሳጣቱ ባሻገር ዘመናዊ የተባለውን አውሮፕላን ባመረተው ቦይንግ ኩባንያ ላይ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችን አስከትሏል። በኩባንያው ላይ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ዋና ሥራ አስፈጻሚውም ከሥራቸው ተባረዋል።

ተመሳሳዩን አውሮፕላን እንዲያመርትላቸው ያዘዙ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶችም ትዕዛዛቸውን ከመሰረዝ አልፈው ሥራ ላይ የነበሩትን ከበረራ ውጪ አደረጓቸው። በዚህም ባለዝናው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ በወራት ጊዜ ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ኪሳራ አጋጠመው።

ጉዳዩም ዛሬም ድረስ መቋጫ አላገኘም።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ጥቁሩ ሳጥን፤ በአውሮፕላኖች ላይ የሚደርስ አደጋን ለሚደረግ ምርመራ ጠቃሚ መረጃን የሚይዝ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ነው።