ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንት ሚኒስትሮችን አባረሩ
የጊኒ ቢሳው ፕሬዚደንት ኡማር ሲሶኮ ኢምባሎ አምስት ሚኒስተሮችን ከሥራ ማባረራቸው ተገለጸ፡፡
የተባረሩት የመከላከያ፣ የውስጥ ጉዳይ፣ የኢኮኖሚ ፣የግብርና እና የኢነርጂ ሚኒስተሮች ሲሆኑ ምክንያቱን በተመለከተ የተሰጠ ማብራሪያ የለም፡፡
ሚኒስተሮቹ የተባረሩት ዛሬ ከሚካሄደው ፖለቲካዊ ጥምረት አገሪቷን ለማስተዳዳር ያለውን መብት በተመለከተ ከሚካሄደው የፓርላማ ክርክር ቀደም ብሎ ነው፡፡
የተባረሩት ሚኒስተሮች የፕሬዚደንት ኢምባሎ ማዴም-15 ፓርቲ አባላት ሲሆኑ ለፕሬዚደንቱም ታማኝ እንደነበሩ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
የዜና ወኪሉ ፕሬዚደንቱ ሚኒስትሮቹን ማባረራቸው በፓርላማው አብላጫ ድምጽ ለማግኘት የተቀየሰ ስልት እንደሆነ ዲታዱራ ዲ ኮንሰንሶ የተሰኘ ድረ- ገጽን ጠቅሶ ጽፏል፡፡
አገሪቷ ለበርካታ ዓመታት በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች፡፡
ፕሬዚደንት ኢምባሎ ታህሳስ ወር ላይ በተካሄደው ምርጫ እንዳሸነፉ አሳውቀው የነበረ ቢሆንም አገሪቷን ለረዥም ጊዜ የመራው ገዥ ፓርቲ ግን ምርጫው ፍትሃዊ እንዳልነበር ገልጿል፡፡
በጊኒ ቢሳው ከጎርጎሮሳውያኑ 1980 ጀምሮ ዘጠኝ ያህል መፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡
የቀድሞው የጦር ጀነራል የሆኑት ኢምባሎ በአገሪቷ ያለውን ውጥረት ለማርገብና አገራቸውን ዘመናዊ ለማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
'ጀነራሉ' በመባል የሚታወቁት የተቃዋሚ ተመራጭ እና የቀድሞ የአገሪቷ የጦር አዛዥ የነበሩት ኢምባሎ፤ ከአውሮፓዊያኑ 2016 እስከ 2018 ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።