«የሕዳሴው ግድብ ለግብፅና ሱዳንም ይጠቅማል» ጥቁር አሜሪካውያን ፖለቲከኞች

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ስምምነት ላይ ያልደረሰቡትን የአባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም በተመለከ ጥቁር የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት መግለጫ አውጥተዋል።

በቅፅል ስሙ ሲቢኤስ የሚል መጠሪያ ያለው የጥቁር አሜሪካውያን የኮንግረስ አባላት ኮውከስ ሶስቱ ሃገራት በመሃላቸው ያለውን ጡዘት እንዲያረግቡት ጥያቄ አቅርቧል።

መግለጫው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ትብብራቸውን እንዲቀጥሉበትና ችግራቸውን በድርድር እንዲፈቱ አሳስቧል። ሃገራቱ በጋራ ተጠቃሚነት ተማምነው በዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት በመጓዝ ከመፍትሔ እንዲደርሱ አባላቱ አሳስበዋል።

በፈረንጆቹ 2011 ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከቀጣናው አልፎ በአፍሪካ ትልቁ ኤሌክትሪክ አመንጪ ግድብ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ፕሮጀክቱ እስከ 6 ሺህ ሜጋዋት ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለጎረቤት ሃገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈል እንድትችል አቅም ይሰጣታል።

የጥቁር አሜሪካውያን ኮንግረስ አባላት ኮውከስ ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎች ዓለም አቀፍ አካላት በ2015 ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የገቡትን የስምምነት ሰነድ እንዲያከብሩ ጠይቋል። አልፎም እኒህ አካላት ጉዳዩን ከአፍሪካ ሕብረትና በቀጣናው ከሚገኙ ዲፕሎማቶች ጋር በመተባበር ለመፍታት እንዲሞክሩ አሳስቧል።

በተለይ ደግሞ ይላል መግለጫው፤ በተለይ ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት በሶስቱ ሃገራት መካከል የሚደረገው ሰላማዊ ስምምነት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ አንድ ወገንን ብቻ የሚጠቅም አለመሆኑን ማረጋገጥ ይገባዋል።

'የሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት የአባይ ወንዝ ፍሰት፣ የኃይል አቅርቦት እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የምግብ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ አለው። የግብፅ ሕዝብ ቁጥር 100 ሚሊዮን እየተጠጋ በመሆኑ የሕዳሴው ግድብ በናይል ወንዝ ላይ ያለውን ጫና በመቀነስ ለግብፅ ሕዝብ የተሻለ የውኃ አቅርቦት ሊያመጣ ይችላል። ኢትዮጵያ ደግሞ 20 በመቶ ሕዝቧን ሊጎዳ ይችላል ተብሎ የተገመተ የድርቅ አደጋ ተደግኖባታል። አልፎም በቅርቡ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ 80 ሺህ አክር [ከ32 ሺህ ሄክታር በላይ] መሬት ላይ የሰፈረ ሰብል ጎድቷል። በሌላ በኩል ሱዳን ከሕዳሴው ግድብ ልትጠቀም ትችላለች። ግድቡ የውሃ ፍሰትን ይመጥናል፣ ደለል ያስቀራል፣ የግብርና ፕሮጀክቶቹን ያስፋፋል፣ እንዲሁም ከውሃ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ይሰጣታል።'

መግለጫው በመጨረሻም፤ የሕዳሴው ግድብ በሁሉም ሃገራት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ያለው፤ የምግብ አቅርቦትን የሚያሻሽል፣ ኃይል የሚያመነጭ፣ ንፁህ ውሃ የሚያቀርብና የቀጣናውን ምጣኔ ኃብት የሚያጎለብት ነው ብሏል።

'የጥቁር አሜሪካውያን ኮንግረስ አባላት ኮውከስ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሰላማዊ ውይይቶችን ይደግፋል፤ ለአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች አካላት አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስምምነት ጠረጴዛ ላይ እንዲቀርብ ይጥራል' የመግለጫው መቋጫ ነው።

የኮውከሱ አባል የሆኑት የአሜሪካ ሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት አባሉ ስቲቨን ሆርስፈርድ ከጥቂት ወራት በፊት አሜሪካ ሚዛናዊ የሆነ ሚና እንድትጫወት ማሳሰባቸው አይዘነጋም።

እንደራሴ ስቲቨን የአሜሪካው የገንዘብ ሚኒስትር ስቲቨን ሚኑቺንን በጥያቄ ባፋጠጡበት ወቅት ነው ይህን ያሉት።