ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጄነራል ሰዓረ እና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ የችሎት ክርክር ለቤተሰብ ክፍት እንዲሆን ተፈቀደ
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ እንዳስታወቀው በጀነራል ሰዓረ መኮንን እና በሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ የግድያ ወንጀል ችሎት ለቤተሰቦቻቸው ክፍት እንዲሆን መፈቀዱን አስታውቋል።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጀነራል ሰዓረ መኮንን እና በሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ የግድያ ወንጀል ሲካሄድ የነበረው የክርክር ሂደት እንዲቀጥል መወሰኑም ተገልጿል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 17 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ፍርድ ቤቶች በከፊል በመዘጋታቸው ክርክሩ ለጊዜው ተቋርጦ የነበረው ክርክር የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንዲቀጥል አቤቱታ በማቅረቡ የምስክር መስማቱን ሂደት ተከሳሽ በማረሚያ ቤት ሆኖ በፕላዝማ እየታገዘ እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የጀነራል ሰዓረ እና ሜ/ጀነራል ገዛኢ ቤተሰቦች በማኅበራዊ ሚድያ ከሚሰሙት ውጪ ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ግድያው ከተፈጸመ አንድ ዓመት የሞላው ቢሆንም ጉዳዩ በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠው የሚናገሩት የጀነራል ሰዓረ ባለቤት ኮሎኔል ጽጌ አለማየሁ፣ "ሰዓረ፤ ጠበቃ እና ጠያቂ ያጣ ሰው ነው። የሚቆምለት ሰው የለውም፤ እኛ አቅም የለንም። ከእኔ አቅም በላይ ነው። ማን ጋር ተሂዶ አቤት እንደሚባልም አላውቅም፤ ጨንቆኛል" ብለው ነበር።
የሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራ ባለቤትም፣ ". . .ሰዓረ እና ገዛኢ ትልልቅ መሪዎች ናቸው። የአገሪቱ ጀነራሎች ናቸው። በሥራ ላይ እያሉ ነው የተገደሉት። የፌደራል መንግሥት፣ የመከላከያ እና ደኅንነት ባለበት አገር ትልልቅ መሪዎች ማን ገደላቸው? ለምን? መልስ ማግኘት ይገባን ነበር። ለቤተሰቡ ዝምታው ከግድያው በላይ ነው የሆነብን . . ." ብለው ነበር።
አክለውም "የማውቀውና ያነጋገረኝ ባለስልጣን የለም፤ እንደተጎዳን፣ ጥቃት እንደደረሰብን፣ ያን የመሰለ ሰው አጥተን በጭንቀትና በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ እንዳለን ተረድቶ አይዟችሁ ያለን የለም፡፡ . . . የሚጠይቀኝ ባገኝ የሚሰማኝን እናገር ነበር. . . የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደን" በማለት ታጋይ አበባ ዘሚካኤል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የችሎት ክርክሩ ሂደት ከሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ባሉት ቀናት የተጎጂ ቤተሰቦች እና ጉዳዩን መከታተል የሚፈልጉ ውስን ሚዲያዎች ወይም ግለሰቦች ባሉበት እንደሚቀጥልም ተገልጿል።