ኮሮናቫይረስ፡ ወረርሽኙ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነባት የመን

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በየመን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ የሚደረገው ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ህጻናት ለከፋ ረሃብ ሊዳረጉ ይችላሉ ሲል የተባበሩት መንግሥታት አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት አስታወቀ፡፡
ዩኒሴፍ በዓለማችን ከፍተኛ በሆነው የሰብዓዊ ቀውስ በምትናጠው የመን ያሉ ህጻናትን ለመታደግ ግማሽ ቢሊየን ዶላር ያስፈልገኛል ብሏል፡፡
ይሁን እንጅ እስካሁን የተቀበለው የገንዘብ ድጋፍ ከሚፈልገው ከግማሽ ያነሰ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ለአምስት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት በፈራረሰችው የመን፤ ሁለት ሚሊየን የሚጠጉ ህጻናት በምግብ እጥረት የተጎዱ ናቸው፡፡
በመሆኑም ድርጅቱ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ 54.5 ሚሊየን ዶላር ማግኘት ካልቻለ፤ 23 ሺህ 500 የሚሆኑ በከፋ የምግብ እጥረት የተጎዱ ህጻናት ለሞት የመዳረጋቸው አደጋ ይጨምራል ብሏል፡፡
በሚሊየን የሚቆጠሩ ህጻናትም ተመጣጣኝ ምግብ እና ቫይታሚን ወይም ክትባት አያገኙም ሲል አሳስቧል፡፡
አክሎም ድጋፉን ማግኘት ካልተቻለ 1 ሚሊየን ነፍሰ ጡር አሊያም የሚያጠቡ እናቶችን ጨምሮ 19 ሚሊየን ሰዎች የጤና አገልግሎት እንደማያገኙ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በየመን የድርጅቱ ተወካይ የሆኑት ሳራ ቤይሶሎው፤ "ህጻናት የዓለማችን ሰብዓዊ ቀውስ ባለበት እና ከኮቪድ -19 ጋር በሚደረግ ትግል ውስጥ ያሉ እንደመሆናቸው፤ ችግሩን አቅልለን ማየት አንችልም" ብለዋል፡፡
በመሆኑም "የገንዘብ ድጋፉን በአፋጣኝ ማግኘት ካልቻልን፤ ህጻናት ለከፋ ርሃብ ይዳረጋሉ፤ በርካቶችም ይሞታሉ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ግብረ ሰናይ ድርጅቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋትም ተጨማሪ 53 ሚሊየን ዶላር እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡
በየመን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ባሉ ግዛቶች ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 288 ሞቶች ተመዝግቧል፡፡
በአማጺያን ቁጥጥር ሥር ባሉት አካባቢዎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ጥቂት ቢሆንም ቁጥሩ ከተጠቀሰው በላይ እንደሚሆን ይታመናል፡፡
በአገሪቷ ላለፉት አምስት ዓመታት የዘለቀው ግጭት በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ቫይረሱን ለመከላከል ወሳኝ የሆኑ ተገቢ የጤና አገልግሎት፣ ንጹህ ውሃ፣ ወይም ንጽህና እንዳያገኙ አድርጓቸዋል፡፡
የአገሪቷ የጤና ሥርዓትም የፈራረሰ ሲሆን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም የለውም፡፡












