አሜሪካ ውስጥ አባት በቀጥታ ውይይት ላይ ሳሉ በልጃቸው በስለት ተገደሉ

ዙም የመወያያ መተግበሪያ በስልክ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የ72 ዓመቱ አዛውንት ከ20 ሰዎች ጋር ዙም በተባለው የቪዲዮ የውይይት መድረክ ላይ እያወሩ እንዳሉ ኒው ዮርክ ውስጥ በገዛ ልጻቸው በስለት ተወግተው እንደተገደሉ ፖሊስ አስታወቀ።

ድዋይት ፓወርስ የተባሉት አዛውንትን የ32 ዓመቱ ልጃቸው በስለት ከወጋቸው በኋላ ከቤታቸው በመስኮት ዘሎ ከወንጀሉ ስፍራ አምልጦ ነበር።

ነገር ግን ጥቃቱ ሲፈጸም በቪዲዮው ውይይት ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሰዎች ለፖሊስ ሪፖርት በማድረጋቸው ተጠርጣሪው የአዛውንቱ ልጅ በአንድ ሰዓት ውስጥ ተይዟል።

የሟች አዛውንት ልጅ ቶማስ ስካሊ ፓወርስ አባቱ ላይ በፈጸመው የግድያ ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል።

ፖሊስ ስለወንጀሉ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው ተጠርጣሪው በደረሰበት ጉዳት ሆስፒታል መግባቱን ጠቅሶ፤ ግለሰቡ ህክምናውን አጠናቆ ሲወጣ ስለግድያው ተጨማሪ መረጃን እንደሚሰጥ አስታውቋል።

ፖሊስ እንዳለው ሐሙስ ዕለት ሟች ከበርካታ ሰዎች ጋር በቀጥታ የቪዲዮ ውይይት ላይ ሳሉ በስለት ተወግተው ሲወድቁ የውይይቱ ተሳታፊዎች በቀጥታ አይተዋል።

ነገር ግን ተወያዮቹ ለፖሊስ ስለሁኔታው ሪፖርት ቢያደርጉም የሟች ሚስተር ፓወርስ ቤት በትክክል የት እንደሆነ እንዳለ ስለማያውቁ ቦታውን ለማወቅ የተወሰነ ጊዜ ፈጅቶ ነበር።

ሟች ድዋይት ፓወርስ በልጃቸው በስለት ተወግተው በተገደሉበት ጊዜ ሲሳተፉበት የነበረው የ'ዙም' የቀጥታ ቪዲዮ ውይይት ርዕሰ ጉዳይ ምን እንደሆነ አልታወቀ።