ኮሮናቫይረስ፡ ሃብታም አገራት ለምን በቀን ብዙ ሺ ሰው መመርመር አቃታቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቁጥር አሳሳች ነው። አንድ አገር በቫይረሱ 1 ሰው ብቻ ነው የተያዘብኝ ሲል መጠርጠር አይከፋም። 10 ሰዎችን መርምሮ ቢሆንስ? አገራት በቫይረሱ የተያዙ ዜጎቻቸውን ቁጥር ሲጠሩ ቀልጠፍ ብሎ እጅግ አስፈላጊ ጥያቄን መጠየቅ ያሻል።
"ለመሆኑ ስንት ሰው መርምራችሁ ነው?"
አሁን ባለው እውነታ የትኛውም ሃብታም አገር ምልክት ያሳዩ ዜጎችን በሙሉ ወዲያዉን ለመመርመር የሚያችል አቅም አልገነባም። አሜሪካዊያን ለምሳሌ ባለፉት ቀናት ለምርመራ በአማካይ እስከ 3 ሰዓት ይሰለፉ ነበር።
ምርመራ በራሱ ቀላል አልሆነም።
ለመሆኑ የትኞቹ አገራት በቀን ብዙ ዜጎችን ይመረምራሉ?
እንግሊዝን እናስቀድም።
የእንግሊዝ መንግሥት በእንደራሴዎችና በሕዝቡ ግፊት በቀን የሚረምራቸውን ሰዎች ብዛት በብዙ እጥፍ ለመጨመር እየሰራ ይገኛል። ግብ አድርጎ የተነሳውም መቶ ሺህ ሰዎችን በቀን መመርመር ነው።
ለጊዜው አሁን ያለው አቅም 10ሺ አካባቢ ነው። ወደዚህ ቁጥር የተገባውም ሰሞኑን በስንት ትግል ነው።
እንግሊዞች በጀርመን ይቀናሉ። እንዴት ጀርመን በቀን 50ሺ ሰው እየመረመረች እኛ 10ሺ ብቻ እያሉ ይጠይቃሉ፤ ጋዜጠኞችም፤ እንደራሴዎችም ሕዝቡም።
ለመሆኑ እንግሊዝ ለምን በቀን 100ሺ ሰዎችን መመርመር ተሳናት?
በርካታ ቁጥር ያለው ሰው ለመመርመር እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም። ብዙ መሟላት ያለባቸው ግብአቶች አሉ፤ የሰውም የቁስም።
አንደኛ እጅግ ግዙፍና የተቀናጀ ቤተ ሙከራ ያስፈልጋል።
ሁለተኛ ቤተ ሙከራው በተራቀቁና በዘመኑ መሣሪያዎች መዋቀር አለበት።
ሦስተኛ ትክክለኛው የላቦራቶሪ ሪየጄንት (Reagents) ሊኖር ይገባል። ይህም የኬሚካል ውህድን በትኖ የሚፈለገውን የኮሮና ጄኔቲካል ኮድ ለይቶ ለማውጣት የሚረዳ ንጥረ ነገር ነው። ይህ ንጥረ ነገር አለመኖር ብዙ አገራት በቀን ብዙ ምርመራ እንዳያደርጉ አንቆ ይዟቸዋል።
አራተኛው አስፈላጊ ግብአት የሰው ኃይል ነው። በበቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል በመቶ ሺዎች ማግኘት ለየትኛውም አገር ቀላል አይደለም።
ከመቶ ሺዎች ከጉሮሮና አፍንጫ የፈሳሽ ናሙና መውሰድ ( Swabs) በቀላሉና በፍጥነት የሚሠራ ተግባር ነው ማለት ይከብዳል። ይህ ቢሳካ ራሱ ናሙናውን በቤተ ሙከራ በፍጥነት አስገብቶ መመርመርም ሰፊ ጊዜና ጉልበት ይጠይቃል።
ይህንን ሁሉ ለማቀናጀት ደግሞ እጅግ ውጤታማ ሎጂስቲክ መዘርጋት የግድ ነው።
ሌላው የምርመራ መንገድ ሰውነት ጸረ ባእድ ነገር ተዋጊ (Antibody) ማምረቱን ለማወቅ የሚካሄደው የደም ምርማራ ነው። ይህም ቫይረሱ ከዚህ ቀደም በሰውነት ላይ ገብቶ ከነበረ ጥቆማን ይሰጣል። ይህንን ዘዴ በብዙ መቶ ሺ ቁጥር ማካሄድ ፈታኝ ነው።
በእንግሊዝ መጀመርያ ምርመራዎች ይካሄዱ የነበረው በጥቂት የሕዝብ ጤና ጣቢያዎች ውስጥ ብቻ ነበር፤ ባለፉት 15 ቀናት ደግሞ 40 በሚሆኑ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት ቤተ ሙከራዎች ውስጥ እየተካሄደ ነው።
በቀጣይም የግል የሕክምና ጣቢያዎችን በዚሁ ሂደት ለማካተት እየተሰራ ነው።
እንግሊዝ እጅግ ግዙፍ የመድኃኒትና ባዮሜዲካል ኢንዱስትሪዎች ያሏት አገር ናት፤ ሆኖም እነዚህ በተገቢው ተግባር ላይ ውለዋል ለማለት አያስደፍርም ይላሉ ዶ/ር ሩፐርት የተባሉ የኮሮና ቫይረስ ተመራማሪ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰሞኑ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ማት ሃንኮክ መቀመጫቸውን እንግሊዝ ላደረጉት ግላክሶስሚዝና አስትራዜኔካ የተባሉት ግዙፍ መድኃኒት አምራቾች የውህድ መነጠያ ንጥረ ነገር ወይም ሬየጀንት እንዲያመርቱ አዝዘዋል።
ይህ ለቤተ ሙከራ እጅግ አስፈላጊው ንጥረ ነገር ኮሮናን ተከትሎ በመላው ዓለም ተፈላጊነቱ እጅግ ጨምሯል። ብዙዎች በመቶ ሺህዎች ምርመራ ለማድረግ እንዳይችሉ ያደረጋቸውም ይኸው ነው።
እንግሊዝ በሚቀጥሉት ሳምንታት በቀን ከ50ሺ በላይ ሰዎችን ለመመርመር ሌት ተቀን እየሠራች እንደሆነ አስታውቃለች።
የትኞቹ አገራት ብዙ ዜጋን መረመሩ?
በቀን በርካታ ዜጎችን ከመረመሩ አገራት ተርታ ጀርመንና ደቡብ ኮሪያ ከፊት ይጠቀሳሉ። ገና ከጅምሩ ነው ቤተ ሙከራዎቻቸውን ዝግጁ አድርገው የጠበቁት።
በተለይ ደቡቡ ኮሪያ በጎዳናዎች ላይ ዜጎች ግር ብለው ምርመራ የሚያካሄዱባቸውን ጊዜያዊ ቤተሙከራዎች በመገንባት ፈጣን እርምጃን መወሰዷ ይነገራል። ለቤተ ሙከራ የሚያስፈልገውን ውህድም በፈጣን ሁኔታ መሰብሰብና ማምረትም ችላለች።
ጀርመን ወትሮም በሕክምናና ተያያዥ ኢንዱስትሪዎች ያላትን የበላይነት አስጠብቃ በቂ ዝግጅትና እርምጃ ወስዳለች። ከዚህም ባሻገር ወረርሽኙን ተከትሎ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አገልግሎት ላይ አውላለች።
ፕሮፌሰር ጆን ነውተን የማኅበረሰብ ጤና ላይ ተመራማሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት አሁን አገራትና የመመርመር አቅማቸውን ስንመለከት ከወረርሽኙ በፊት ያላቸውን ዝግጁነትና አቅም ነው የሚነግረን ይላሉ።
ይህን ሲያስረዱም ደቡብ ኮሪያ ለምሳሌ የቫይሮሎጂ ቤተሙከራዎችን ያዘጋጀችው ገና ድሮ በፈረንጆች 2003 ሳርስ ወረርሽኝ በተቀሰቀሰበት ጊዜ ነው። ጀርመን ድሮም በሕክምናና ቤተ ሙከራዎቿ ትልቅ አቅምን የገነባች የዓለም አገር ናት።
እንግሊዝ እስከዛሬ የመረመረቻቸው ሰዎች ቁጥር 200 ሺ እንኳን አልሞላም። ጀርመን በበኩሏ በሳምንት 500ሺህ ሰዎችን የመመርመር አቅም ላይ ደርሳለች።
አይደለምና ጤንነት የሚሰማው መደበኛ ዜጋ፣ ምልክቾቹን የሚያሳዩ ዜጎች ሳይቀሩ ለምርመራ ፍላጎት ቢኖራቸውም ይህን እድል በቀላሉ ማግኘት አልቻሉም።
በብዙ ቁጥር መመርመር ፋይዳው ምንድነው?
ምርመራ የሚካሄድበት ሁለት ዓላማ አለ፤ አንዱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቶሎ የመለየትና ገለል የማድረግ ግብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ምልክት ሳያሳዩ ቫይረሱ ይዟቸው የነበሩና የዳኑ ሰዎች ካሉ እነርሱን ለይቶ ለመመዝገብ ነው።
ቶሎ ብዙ ቁጥር ያለው ዜጋን መመርመር የጽኑ ሕሙማን ክፍልን በአፋጣኝ ለማዘጋጀት፤ የሚያስፈልጉ ቬንትሌተሮችን ቁጥር ለመወሰንና ለማቅረብም ወሳኝ ነው።
ከዚህም ባሻገር የጤና አስተዳደሮች የት አካባቢ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴን ማገድ እንደሚኖርባቸውና የት አካባቢ ይህ መመሪያ ሊላላ እንደሚገባ ሊያውቁ የሚችሉትም በተወሰኑ አካባቢዎች በርካታ ሰዎችን በመመርመርና የስርጭቱን ስፋት ቶሎ በመገንዘብ ነው።
ለምሳሌ በአንድ አካባቢ በበቂ ሁኔታ ምርመራ ሳይደረግ ሰዎች ከቤታቸው እንዳይንቀሳቀሱ ሊታገዱ ይችላሉ። ይሄ ምጣኔ ሀብትን ያደቃል። ምናልባት ምርመራ ቢደረግ በዚያ አካባቢ ምንም አይነት ስጋት እንደሌለ መረዳት ይቻል ይሆናል።
ጀርመን ወረርሽኙ ከጀመረ ወዲህ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን መርምራለች።
ፈረንሳይ በበኩሏ እስከዛሬ በጠቅላላው ከመቶ አምሳ ሺ ላነሱ ዜጎች ብቻ ነው ምርመራ ማድረግ የቻለችው። እንግሊዝ ከዚህ ጥቂት ከፍ ያለ ቁጥር ነው ማሳካት የቻለችው።
ፈረንሳይ በሰኔ ወር 100ሺ ሰው በቀን ለመመርመር እየተዘጋጀሁ ነው ብላለች። አሁን በቀን ከ30ሺህ ያነሰ ነው የምትመረምረው።
ስፔን በበኩሏ ከ15ሺ እስከ 20ሺ ሰዎችን በቀን መመርመር ጀምራለች። ስፔን ከቻይና የመጡ መመርመሪያዎች ብላሽ ሆነው አግኝቻቸው እንጂ ከዚህም በላይ በቀን መመርመር እንችል ነበር ብላለች።
ጣሊያን በበኩሏ በጠቅላላው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መርምራለች።
በኮሮና ክፉኛ የተጠቃችው አሜሪካ በበኩሏ እስካሁን ከ1.3 ሚሊዮን ሰዎችን መርምራለች፤ በቀን የመመርመር አቅሟም ከመቶ ሺ ከፍ ያለ ነው።















