ኮሮናቫይረስ፡ ከቤት የሚወጡትን ለመቆጣጠር ቱኒዚያ የሮቦት ፖሊስ አሰማራች

የፎቶው ባለመብት, AFP
በቱኒዚያን ዋና ከተማ፤ ቱኒዝ መንግሥት ያስቀመጠውን ቤት የመቀመጥ ገደብ ተፈፃሚነት ለመከታተል ሮቦት ፖሊሶች ተሰማሩ።
ጭር ባሉት የቱኒዝ ጎዳናዎች ድንገት ብቅ ካሉና እነዚህ ሮቦት ፖሊሶች ካገኙዎ ጠጋ ብለው ወዴት? እንዴት? ብለው ይመረምሩዎታል።
ያ ብቻ ሳይሆን ለሮቦቱ መታወቂያና ሌሎች የሚጠየቁትን መረጃዎች ማሳየት ይጠበቅብዎታል። ከዚያም ቢሮ ተቀምጦ ሮቦቶቹን የሚቆጣጠረው የፖሊስ ባልደረባ ያቀረቡትን ማስረጃ ያጣራል።
በቱኒዚያ ቤት ውስጥ የመቀመጥ መመሪያው ከተላለፈ ሁለት ሳምንት ሞልቶታል። በአገሪቱ እስካሁን ድረስ በኮሮናቫይረስ ምክንያት 14 ሰዎች ሲሞቱ 436 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡ ተገልጿል።
በቱኒዚያ በተጣለው ቤት ውስጥ የመቀመጥ መመሪያ መሰረት ከሆነ ማንኛውም ሰው አስፈላጊ ቁሳቁሶችን አልያም መድኃኒት ለመግዛት ካልሆነ በስተቀር ከቤቱ ውልፊት ማለት አይኖርበትም።
በቱኒዚያውያን የተሰራ ነው የተባለለት ይህ ፖሊስ ሮቦት ወይንም በእነሱ አጠራር ፒጋርድ፤ ወደ መስክ ሥራ ለመሰማራት ግዳጁን የተቀበለው ከአገር ውስጥ ሚኒስቴር ነው ተብሏል።
በቁጥር ምን ያህል ሮቦቶች እንደተሰማሩ ግን አልተገለፀም።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ሮቦቱን የሰራው ኢኖቫ ሮቦቲክስ ለቢቢሲ ጉዳዩ ሚስጥራዊ ነው ሲል ገልጿል። በተጨማሪም ምን ያህል ወጣበት የሚለውን ጥያቄም ከመመለስ ታቅቧል።
ባለ አራት እግሩ ፒጋርድ እንደ ራዳር መስራት የሚያስችለው ካሜራና በጨረር የመለየት ቴክኖሎጂ ተገጥሞለታል።
የአገር ውስጥ ሚኒስትር በፌስቡክ ገጹ ላይ ስለሮቦቱ ተግባር የሚያሳይ አጭር ተንቀሳቃሽ ምስል አጋርቶ ነበር።
አንዳንድ ቱኒዚያውያን የሮቦቱን ተግባር ሲያደንቁት ሌሎች ደግሞ ተግባሩን ለማከናወን ይንቀራፈፋል ሲሉ አጣጥለውታል።
በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ተጠቃሚዎች ዘንድ ይህ ሮቦት ፖሊስ በርካታ ቤት የመቀመጥ እገዳውን ጥሰው የወጡ ሰዎችን ሲያስቆምና ሲጠይቅ የሚያሳዩ ምስሎች ተጋርተዋል።
ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት የኢኖቫ ደንበኞች ትልልቅ የግል ድርጅቶች የነበሩ ሲሆን ድርጅቱም "የጤና ክብካቤ" ላይ የሚሳተፉ ሮቦቶችን ነበር የሚያመርተው።
በአሁኑ ወቅትም በቱኒዝ ሆስፒታል ውስጥ በቅርቡ ሥራ የሚጀምርና የሕክምና ባለሙያዎችንና የህሙማንን ንክኪ የሚቀንስ ሮቦት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዘመን ሮቦቶችና አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የተለያዩ የመከላከል ተግባራት ላይ በቻይና እና በሌሎች አገራት ተሳትፈው ታይተዋል።














