ኮሮናቫይረስ፡ ተስፋ ቢኖርም ይህ ሳምንት ለአሜሪካ አደገኛው ይሆናል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ ባጠቃቸው ቦታዎች ላይ ለውጦች መታየታቸውን ተከትሎ በሽታውን ለማስቆም ተስፋ እንዳለ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ።
ትናንት እሁድ በአሜሪካ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ዋነኛ ማዕከል በሆነችው የኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መቀነሱም ተነግሯል።
ምንም እንኳን ፕሬዝዳንቱ ይህ የቁጥር መቀነስ "ጥሩ ምልክት" እንደሆነ ቢናገሩም፤ ወረርሽኙ በአሜሪካ ከፍተኛው ደረጃ ላይ እየደረሰ በመሆኑ ተጨማሪ ሞት ሊያጋጥም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
"በመጪዎቹ ቀናት አሜሪካ የዚህን ወረርሽኝ ከፍተኛው ጉዳት ሊያጋጥማት ይችላል" ሲሉ በጽህፈት ቤታቸው በየዕለቱ በኮሮናቫይረስ ላይ በሚሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
የአፍና ፊት መሸፈኛ ጭንብልና የመተንፈሻ መሳሪያዎችን ጨምሮ የህክምና ባለሙያዎችና መገልገያዎች በበሽታው ክፉኛ ወደ ተጠቁትና ከፍተኛ ድጋፍን ወደሚፈልጉት ግዛቶች እንደሚላኩ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንቱ የኮሮናቫይረስ ግብረ ኃይል አባል የሆኑት ዴብራ ቢርክስ እንዳሉት በወረርሽኙ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በቅርብ ቀናት ውስጥ እየቀነሰ ባለባቸው ጣሊያንና ስፔን ውስጥ የሚታየው "ወደፊት በሚኖረው ሁኔታ ላይ ተስፋን የሚሰጥ ነው" ብለዋል።
በፕሬዝዳንቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት ዶክተር ቢርክስ "ከበርካታ ሳምንታት በፊት ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያለው የበሽታው መስፋፋት በሚቀጥለው ሳምንት ሊረጋጋ እንደሚችል ተስፋ" መኖሩን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ወረርሽኝ "በጣም መጥፎ ነው" ያሉት የፕሬዝዳንቱ ዋነኛ የጤና አማካሪ ዶክትር አንተኒ ፋውቺ እንዲሁም ሌሎች ባለሙያዎች የፕሬዝዳንቱና የዶክተሯ የታያቸውን ተስፋ ጋር አይስማሙም።
ነገር ግን ዶክትር አንተኒ ፋውቺ እንዳስጠነቀቁት "ይህ ሳምንት በአብዛኞቹ አሜሪካዊያን ህይወት ውስጥ ከባዱና አሳዛኙ ሳምንት ይሆናል።"
"ይህ ሳምንት በታሪካችን ከባድ ጉዳት እንደደረሱበት የፐርል ሃርበርና የመስከረም 11ዱ ጥቃቶች ያህል ይሆናል" በማለት ለፎክስ ኒውስ የተናገሩት ደግሞ ዋነኛው ሐኪም ጄሮም አዳምስ ናቸው።
አሜሪካ እስካሁን ድረስ ከ337 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውንና 9,619 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው ማለፉን ሪፖርት አድርጋለች። ይህም በዓለም ላይ ከፍተኛ በኮቪድ-19 የተያዙና የሞቱ ሰዎች ቁጥር ነው።














