በስፔን የሟቾች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም የእንቅስቃሴ ገደቡ ይቆያል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስት ፔድሮ ሳንቼዝ በአገራቸው ለተከታታይ ሁለት ቀናት በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር መቀነሱን ተከትሎ "የሽታው ከፍተኛ መጠን ላይ ደርሰናል" ሲሉ ተናገሩ።
ሳንቼዝ አክለውም በቤት ውስጥ የመቀመጡ መመሪያ ለቀጣዮቹ 20 ቀናት እንደተራዘመ ያስታወቁ ሲሆን ገደቡ "ሕይወትን ይታደጋል" ብለዋል።
ይህ ሳምንት በቀን 809 ሰዎች የሞቱበት ዝቅተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።
በተያያዘ የስፔን ባለስልጣናት የአገሪቱ ሕዝብ ላይ የተጣለውን ደንብ ለማላላት ለእያንዳንዱ ግለሰብ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ለማግኘት እየጣሩ ነው።
በስፔን በአሁኑ ወቅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማግኘት አዳጋች ነው።
መንግሥት ከዚህ ቀደም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ከሆስፒታል ውጪ ያለው ግልጋሎት እምብዛም ነው ሲል ተናግሮ ነበር።
ይሁን እንጂ አሜሪካ አርብ ዕለት በማንኛውም ስፍራ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን ከመከረች ወዲህ በምዕራቡ ዓለም ያለው አቋም እየተቀየረ መጥቷል።
ኦስትሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ እስራኤል፣ ቱርክ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ መሆኑን ደንግገዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ 1.1 ሚሊዮን ሰዎች በኮቪድ-19 ሲያዙ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሰቲ መረጃ ያሳያል።
በስፔን ባለፉት 24 ሰዓታት 7,026 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ይህም አርብ ዕለት ከነበረው 7,472 ቁጥር የቀነሰ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም እስካሁን ድረስ 11,744 ሰዎች በኮቪድ-19 የተነሳ የሞቱ ሲሆን አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ በጣሊያን ካለው በልጦ 124,736 መሆኑ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ ለሁለት ሳምንት ቤት የመቀመጥ እገዳውን ሲያራዝሙ ይህ ውሳኔ የጤና ባለሙያዎች እንዲያገግሙ ይረዳቸዋል ብለዋል።
አክለውም አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር መቆጣጠር ከተቻለ "ወደ አዲሱ ሕይወት በፍጥነት በመመለስ" ኢኮኖሚያችንን ዳግም መገንባት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
ሳንቼዝ አዲሱ ሕይወት ያሉት አዲስ የንጽህና አጠባበቅ መመሪያ፣ እንዲሁም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን የመለየት ተግባር እንደሚዘረጋ ለመግለጽ መሆኑን ጨምረው አስታውቀዋል።
የአውሮፓ ሕብረትም ምጣኔ ሃብታዊ ተግዳሮትን በጋራ እንዲታገል "አውሮፓ በዚህ ሰዓት መውደቅ የለባትም" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
"የስፔን ምጣኔ ሃብት ኪሳራ ውስጥ እንደሚወድቅ እሙን ነው፤ ስለዚህም ቫይረሱን ለመዋጋት ከሚመጣው ትውልድ ሃብት መውሰድ አለብን" ብለዋል።
እስካሁን ድረስ ስፔን፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይና ሌሎች አገራት ለአውሮፓ ሕብረት፤ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የገጠማቸውን ኪሳራ ለመጋራት ጥሪ ቢያቀርቡም ሕብረቱ ግን በቀረበው እቅድ ላይ መስማማት አልቻለም።














