ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መሆኑ ታወጀ

የዓለም ጤና ድርጅት ዛሬ ምሽት ዓለምን እያስጨነቀ ያለውን የኮሮናቫይረስ በሽታ "ወረርሽኝ" መሆኑን አውጇል።

አንድ በሽታ ወረርሽኝ የሚባለው በዓለም ዙሪያ በተመሳሳይ ጊዜ በተለያዩ አገራት ውስጥ ሲሰራጭ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዳሉት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከቻይና ውጪ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ13 እጥፍ ጨምሯል።

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ጨምረውም በሽታውን በተመለከተ እርምጃ ለመውሰድ የታየው ቸልተኝነት "በጣም እንዳሳሰባቸው" ተናግረዋል። በሽታው ወረርሽኝ ተብሎ መሰየሙ የዓለም የጤና ድርጅት በሽታውን በተመለከተ አገራት ማድረግ ይገባቸዋል ብሎ የመከራቸው ነገሮች ይቀየራሉ ማለት እንዳልሆነ አመልክተዋል።

መንግሥታት የወረርሽኙን ፍጥነት ለመግታት የሚወስዱትን እርምጃ የበለጠ ቀልጣፋ በማድረግ "አስቸኳይና ፋታ የማይሰጥ" ሊያደርጉት ይገባል ብለዋል።

"በርካታ አገራትም ይህ ቫይረስ ባለበት ለማስቆምና ለመቆጣጠር የሚቻል እንደሆነ አስመስክረዋል" ሲሉ ዶክተር ቴድሮስ ተናግረዋል።

በሽታው በስፋት የሚተላለፍበት ሁኔታ ባጋጠማቸው አገራት ውስጥ ተመሳሳይ ነገርን ለማከናወን ይቻል እንደሆነ ማረጋገጥ ዋነኛው ፈተና መሆኑንም ገልጸዋል።

ጨምረውም መንግሥታት "የዜጎችን ጤና በመጠበቅ፣ የአገልግሎት መቋረጥን በመቆጣጠርና ለሰዎች ሕይወት ክብር በመስጠት" መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ ነበረባቸው ብለዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት ቻይና ውስጥ የተቀሰቀስው ይህ በሽታ በርካታ አገራትን በማዳረስ እስካሁን ድረስ ከ4366 በላይ ሰዎችን ሲገድል በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ደግሞ ከ122 ሺህ በላይ ሆኗል።