የማንችስተር ሲቲና የአርሰናል ግጥሚያ በኮሮናቫይረስ ስጋት ለሌላ ጊዜ ተላለፈ

ማንችስተር ሲቲ ከአርሰናል ጋር ዛሬ እሮብ፤ ሊያደርግ የነበረው የፕሮሪሚየር ሊግ ጨዋታ "ቅድመ ጥንቃቄ" በሚልና በርካታ የአርሰናል ተጫዋቾች ራሳቸውን ለይተው በመቀመጣቸው የተነሳ ለሌላ ጊዜ ተላለፈ።

የመድፈኞቹ ተጫዋቾች ራሳቸውን አግልለው በር ዘግተው የተቀመጡት የኦሎምፒያኮስ ባለቤት የሆኑት ኢቫንጀሎስ ማሪናኪስ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ ነው።

አርሰናል እንዳለው ከሆነ ማሪናኪስ ከሁለት ሳምንት በፊት በነበረው አውሮፓ ሊግ ጨዋታ ወቅት በርካታ ተጫዋቾችን አግኝተው ነበር።

የ52 ዓመቱ ማሪናኪስ በኮቪድ 19 [ኮሮናቫይረስ] መያዛቸውን የተናገሩት ማክሰኞ ዕለት ነበር።

ኦሎምፒያኮስ በአውሮፓ ሊግ ዎልቭስን ሐሙስ ዕለት የሚያስተናግድ ሲሆን፤ ዎልቭስ ግን አስቀድሞ ጨዋታው እንዲራዘምለት ጠይቆ የነበረ ቢሆንም ተከልክሏል።

የፕሪሚየር ሊግ የበላይ ኃላፊዎች ግን ከእንግዲህ ወዲህ ምንም ዓይነት ጨዋታ የማራዘም ሃሳብ እንደሌላቸው ገልፀው "አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ ተወስዷል" ሲሉ ተናግረዋል።

ብራይተን በበኩሉ ከአርሰናል ጋር ያላቸው ግጥሚያ ቅዳሜ እለት በተያዘለት ሰዓት እንደሚካሄድ አስታውቋል።

"ተጫዋቾቹ ራሳቸውን ነጥለው የሚያቆዩበት ጊዜ የሚያበቃው ሐሙስ በመሆኑ አደጋው እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው" ብለዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን ድረስ 382 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ስድስት ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

የኮሮናቫይረስ የስፖርት ውድድሮችን በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳ ሲሆን የጣሊያን ሴሪ አ ሲቋረጥ የፈረንሳይና የስፔን ጨዋታዎች በዝግ ስታዲየም እንዲካሄዱ ተወስኗል።

ማንችስተር ዩናይትድን፣ ሬንጀርስንና ቼልሲን የሚያሳትፈው የአውሮፓ ዋንጫም በሚቀጥሉት ቀናት በኦስትሪያ እና በጀርመን በዝግ ስታዲየሞች ይካሄዳሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም ግን ስፖርት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሲስተጓጎል ይህ የመጀመሪያው ጨዋታ ነው።