የአይፎን ስልክ አምራቹ ኩባንያ ኮሮናቫይረስ መከላከያ ጭምብል ማምረት ሊጀምር ነው

የፎቶው ባለመብት, Foxconn
ግዙፉ ኤሌክትሮኒክስ አምራቹ ፎክስኮን ኮሮናቫይረሰን ለመከላከል ወይም በቀዶ ህክምና ወቅት ሊደረግ የሚችል የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ወይም ጭምብል ሊያመርት መሆኑ ተነግሯል።
የአይፎን ስልክ አምራች ጭምር የሆነው ኩባንያው በኮሮናቫይረስ ምክንያት በቻይና ለመዝጋት የተገደደውን ማምረቻ ጣቢያዎቹን ለመክፍት ጥረት እያደረገ ይገኛል።
የኮሮናቫይረስ መከሰት በመላው ዓለም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ 'ማስክ' እጥረት እንዲያጋጥም አድርጓል።
ፎክስኮን በዚህ ወር መጨረሻ ላይ በቀን ሁለት ሚሊዮን የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛዎችን ለማምረት ማቀዱን አስታውቋል።
"ይህን ወረርሽኝ ስንዋጋ እያንዳንዷ ሰከንድ ትርጉም አላት" ሲል ኩባንያው 'ዊቻት' በተሰኘው ማህብራዊ ሚዲያ ላይ አስፍሯል።
"የመከላከል እርምጃ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ያስችላል። የሰዎችን ህይወት መታደግ መቻል ማለት በፍጥነት ቫይረሱን ማሸነፍ ማለት ነው" ብሏል አይፎን አምራቹ ኩባንያ።
ይህ ኩባንያ የዓለማችን ግዙፉ የኤሌክትሮኒክስ አምራች ሲሆን፤ ከአይፎን በተጨማሪ፣ አይፓድ፣ የአማዞን ኪንድል እና ፕለይስቴሽኖችን ያመርታል።
ኩባንያው በቅድሚያ የሚያመርታቸው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ምርቶች ለሠራተኞቹ እንደሚያድል ከዚያ በኋላ ምርቶቹን ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።













