የሞ ፋራህ የቀድሞ አሠልጣኝ ለአራት ዓመት ከአትሌቲክስ ታገዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሞ ፋራህ ቀድሞ አሠልጣኝ፣ አልቤርቶ ሳላዛር፣ ከአበረታች መድሀኒት ጋር በተያያዘ ከስፖርት ለአራት ዓመት ታገዱ።
የ61 ዓመቱ ሳላዛር የአራት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆነው ፋራህን ማፍራት የቻለው የናይክ ኦሪጎን ፕሮጀክት ከ2011 እስከ 2017 ድረስ ሲመሩ ቆይተዋል።
ውሳኔው የተላለፈው በአሜሪካው የፀረ አበረታች መድሃኒት ኤጀንሲ ለአራት ዓመት ያህል ምርመራ ሲደረግ ከቆየና ለሁለት ዓመት ያህል በፍርድ ቤት ክርክር ከተካሄደ በኋላ ነው።
ምርመራው የተጀመረው ቢቢሲ በ2015 ፓናሮማ የተሰኘ ፕሮግራሙ ላይ ጉዳዩን ካቀረበ በኋላ ነው።
ይህ የቢቢሲ ፕሮግራም ከአሜሪካው ፕሮፑብሊካ ድረገፅ ጋር በጋራ በመሆን በአሜሪካ ኦሪጎን ውስጥ በሚገኘው የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ስፍራ የሚሰጡ አበረታች መድሃኒቶችንና የሚካሄዱ ተገቢ ያልሆነ ተግባራትን አጋልጧል።
የዩኬ ስፖርቶችን የሚቆጣጠረው ዩኬ አትሌቲክስ፣ የራሱን ምርመራ ያካሄደ ሲሆን ለስድስት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮናው፣ እንግሊዛዊው ፋራህ፣ ከ አሜሪካዊው ሳላዛር ጋር እንዲሰራ ይሁንታውን ሰጥቶት ነበር።
በናይክ እየተከፈላቸው በርካታ የሳላዛር አትሌቶችን የሚያክሙት ዶክተር ጄፍሪ ብራውን ደግሞ ለአራት ዓመት ታግደዋል።
ፋራህ ከሳላዛር ጋር የተለያየው በ2017 መሆኑን ጠቅሶ ከአበረታች መድሃኒት ጋር በተያያዘ አለመሆኑን ግን ገልጿል።












