የቡሩንዲ ባለስልጣን የካቶሊክ ቀሳውስትን አወገዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቡሩንዲ ባለስልጣናት አለመቻቻልንና ፖለቲካዊ ጥቃቶችን በማውገዝ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የሃገሪቱ የካቶሊክ ቀሳውስት እንዲወገዙ ጠየቁ።
የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ዊሊ ኒያሚትዌ በትዊትር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት አንዳንድ ቀሳውስት እሳት በሚጭሩ ቃላት "መርዛማ ጥላቻን እየረጩ ነው" ሲሉ ከሰዋቸዋል።
እሁድ ዕለት ከመንግሥት የተለየ አመለካከት ያላቸው ሰዎች እንደሚሳደዱና አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንዳይንቀሳቀሱ እንደተደረጉ የሚገልጽ ከቤተ-ክርስቲያኒቱ የቀሳውስት ጉባኤ የተላለፈ መልዕክት በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እንደተነበበ ተገልጿል።
መልዕክቱን ጠቅሶ ኤኤፍፒ እንደዘገበው "ከመንግሥት የተለየ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ላይ የሚወሰደው ፖለቲካዊ እርምጃ እስከ ግድያ ይደርሳል. . ." እንደሚል ተገልጿል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ቡድን እንዳስጠነቀቀው ሊካሄድ ከታሰበው ምርጫ ቀደም ብሎ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀሎች እየተፈጸሙ መሆኑን ገልጾ ነበር።
ከአራት ዓመት በፊት ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ለሦስተኛ የስልጣን ዘመን በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ተከትሎ በተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ቡሩንዲ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ ነበር።
በክስተቱም ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ አለመረጋጋቱን በመሸሽ 400 ሺህ ሰዎች ሃገሪቱን ጥለው ተሰደዋል።
ምንም እንኳን ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ በቅርቡ ይካሄዳል በሚባለው ምርጫ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸው ቢነገርም ባለፈው ዓመት የሃገሪቱን ሕገ መንግሥት ለማሻሻል በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ ፕሬዝዳንቱ ለቀጣዮቹ 14 ዓመታት በመንበራቸው ላይ እንዲቆዩ ሆኖ ተሻሽሏል።












