ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፡ "ጥገኝነት ፈላጊዎች የማመልከቻ ክፍያ ይፈፅሙ"

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥገኝነት ፈልገው ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች፤ ማመልከቻ ለማቅረብ ክፍያ መፈፀም እንዳለባቸው ተናገሩ። ፕሬዚደንቱ ይህንን አቅጣጫ ያስቀመጡት ባለፈው ሰኞ በፕሬዚደንታዊ የመግባቢያ ሰነድ ላይ ሲሆን አዳዲስ ሕጎች እንዲካተቱ የተጠየቀበት ነው።
ይሁን እንጂ ክፍያ እንዲፈፀም መደረጉ ብዙ ሰዎችን መድረስ አያስችልም የሚል ትችት አጋጥሞታል።
በአሜሪካ የስደተኞችን ጥያቄ የሚያስተናግደው ድርጅት የቀድሞ ኃላፊ ቪክቶሪያ ኔልሰን በበኩላቸው "በአብዛኛው ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች በትከሻቸው ላይ እራፊ ጨርቅ ብቻ አንጠልጥለው ነው የሚመጡት፤ ምንም የላቸውም" ሲሉ አስተያየታቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልፀዋል።
በመግባቢያ ሰነዱ ላይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ክፍያው የስደተኞቹን ማመልከቻ ሂደት ለመከታተል የሚውል እንጂ ከዚያ በላይ ገንዘብ እንደማይጠይቁ የገለፁ ቢሆንም ምን ያህል እንደሚሆን ያስቀመጡት የገንዘብ መጠን የለም።
ነገር ግን አሁን ባለው ሕግ ወደ ሃገሪቱ በሕጋዊም ሆነ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ ጥገኝነት ፈላጊዎች ማመልከቻቸው እስከሚያልቅላቸው ድረስ ጊዜያዊ የሥራ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ይደረጋል።
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት የተለየ ሁኔታ ከሌለ በስተቀር እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች በ180 ቀናት ውስጥ በስደተኞች ፍርድ ቤት ማለቅ የሚቻልበት ሕግ መኖር አለበት ሲሉ ይሞግታሉ።
ቢሆንም ግን ከ800 ሺህ በላይ ጥገኝነት ጠያቂዎች ባሉባት ሃገር በተጠቀሰው ቀነ ገደብ ጥያቄው ተስተናግዶ ያልቃል የሚለው ዘበት ነው። ይህ ማለት ደግሞ ሂደቱን ለመጨረስ አንድ ዓመት ይወስዳል ማለት ነው።
በመሆኑም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለአሜሪካ ፍትህ ቢሮና የሃገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤት የሰጡት ትዕዛዝ አሜሪካ ካላት ፖሊሲ ጋር ሲነፃፀር ተዓምራዊ ለውጥ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የገቡና ጊዜያዊ የሥራ ፈቃድ ያገኙ ስደተኞችን ጥያቄም መሰረዝ እንደሚፈልጉ ፕሬዚዳንቱ የገለፁ ሲሆን ባለሥልጣናቱ አዲስ ሕግ አርቅቀው እንዲመጡ የ90 ቀናት ጊዜ ሰጥተዋል።
ትዕዛዙ በመካከለኛው አሜሪካ የሚመጡ ስደተኞች ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገቡ ለመቆጣጠር ሲሉ ያመጡት ሃሳብ እንደሆነ ተነግሯል።













