"አንድ አትሌት በህይወቱ የሚያስደስተው የአለም ሪከርድን መስበር ነው" ዮሚፍ ቀጀልቻ

አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ ቦስተን ውስጥ በተካሄደ የአንድ ማይል (1.6 ኪሎ ሜትር) የቤት ውስጥ ውድድር ከ22 ዓመታት በፊት በሞሮኳዊው አትሌት ሂሻም አልገሩሽ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ ኢትዮጵያዊው አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ ሰብሮታል።

ከትላንት በስቲያ እሁድ እለት በተደረገው በዚህ የቤት ውስጥ ውድድር 3፡47፡01 በመግባት ሪከርዱን አሻሽሏል።

በዚህ ውድድር ላይ አሜሪካዊው ጆኒ ግሬጎሬክ 3፡49፡98 በመግባት በሁለተኛነት አጠናቋል።

"ሪከርድ መስበር በጣም ደስ ይላል፤ አንድ ሰው የሚሮጠው የሆነ ነገር ለማግኘት ነው።" የሚለው አትሌቱ ለሯጭም ከፍተኛ ደረጃ እንደሆነ ይናገራል።

"አንድ አትሌት በህይወቱ የሚያስደስተው ነገር ኦሎምፒክ ማሸነፍና የአለም ሪከርድ መስበር ነው። ስለዚህ በጣም ደስ ብሎኛል።" በማለት ለቢቢሲ ገልጿል።

ሪከርድ በመስበሩ የሚያገኘው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄም ከዚህ ቀደም ሪከርድ የሚሰብር የሚያገኘውን ያህል እንደሆነ ተናግሯል።

በአልግሩሽ ተይዞ የነበረውን ሬከርድ በአንድ ደቂቃ በአርባ አራት ሰከንዶች ያሻሻለው ዮሚፍ በሶስተኛው ሙከራ ሪከርድ መስበር እንደቻለም ተዘግቧል።

የ21 አመቱ ዮሚፍ ከሶስት ሳምንታት በፊት ኒውዮርክ ውስጥ በተመሳሳይ ርቀት ውድድር ያደረገ ሲሆን፤ በወቅቱም በ0.01 ሴንቲ ሰከንድ ምክንያት ሪከርዱን ሳይሰብር ቀርቷል።

በወቅቱ ስለነበረው ስሜትም አትሌቱ ለቢቢሲ ተናግሯል " ያኔ በጣም ተሰምቶኝ ነበር፤ ውድድሩን ስጨርስ ዝቅ ብየ ቢሆን ኖሮ ሪከርዱን እሰብረው ነበር።" የሚለው አትሌቱ በቀጣይነትም ረጅምና መካከለኛ ርቀት የመሮጥ እቅድ እንዳለው ተናግሯል።

"ትልቁ ሀሳቤ ከቤት ውጭ በአምስት ሺ ሜትር ሪከርድ መስበር ወይም ፈጣን ሰአት ማስመዝገብ እፈልጋለሁ" ብሏል።

ዮሚፍ ያስመዘገበው ሰአት በኢትዮጵያም ውስጥ ፈጣኑ ሲሆን ይህም በአማን ወቴ 3፡48፡60 ተይዞ የነበረውን አሻሽሎታል ማለት ነው።