ታይላንዳዊው የ13 ዓመቱ ቦክሰኛ አኑቻ ኮቻና በቦክስ ውድድር ሳቢያ ሕይወቱ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Facebook
የ13 ዓመቱ ታዳጊ የቦክስ ውድድር ሳቢያ ሕይወቱ ማለፉን ተከትሎ ታይላንድ የህፃናት የቦክስ ውድድርን እንድታግድ የነበሩ ጥያቄዎች በርትተው ቀጥለዋል።
አኑቻ ኮቻና በአንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት ባዘጋጀው ውድድር ላይ ባጋጠመው የጭንቅላት ውስጣዊ ደም መፍሰስ ለሁለት ቀናት ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ሕይወቱ አልፏል።
የታቃራኒ ቡድን አባላት እንደገለፁት ታዳጊዎቹ ራሳቸውን ከአደጋ የሚከላከሉበት ትጥቅ አላጠለቁም ነበር።
በዚህም ሳቢያ በውድድሩ ወቅት ታዳጊው ከመውደቁ በፊት ጭንቅላቱ ላይ መመታቱ ታውቋል።
ታዳጊው ከ8 ዓመት ዕድሜው አንስቶ ቤተሰቦቹን ለመርዳት 170 ግጥሚያዎችን አድርጓል።
በታይላንድ 'ሟይ' ተብሎ የሚጠራው የታዮች የቦክስ ውድድር በአገሪቱ በስፋት የሚታወቅ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ተጋጣሚዎችና ቤተሰቦቻቸው ውድድሩን ገንዘብ የማግኛ መንገድ አድርገውታል።
ይሁን እንጂ ይህንን ስፖርት ለማካሄድ ህጉ ክፍተት እንዳለበት ተደጋግሞ ይነሳል።
በተቃራኒው አንዳንድ ሰዎች ህፃናቱን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲባል ውድድሩን ለማገድ የሚደረገውን ጥረት አስፈላጊ አይደለም ሲሉ ይቃወማሉ፤ ምክንያታቸው ደግሞ በአገሪቱ ያለው ባህላዊ የቦክስ ውድድር አካል መሆን አለባቸው የሚል ነው።
ይሁን እንጂ የጉዳዩን አደገኝነት ያሳሰበው የታይ ምክርቤትም ከ12 ዓመት በታች የቦክስ ውድድርን ለማገድ ህጉን እየመረመሩ ይገኛሉ።
በታዳጊው አኑቻ ህልፈት በርካታ የታይ ነዋሪዎች አዝነዋል፤ በመካከለኛው ሳሙት ፕራካን ግዛት የተደረገው ውድድር ላይ የተነሳውን የቦክሰኛውን ምስል በመጋራት ሀዘናቸውን እየገለፁ ነው።
በርካታ ቁጥር ያላቸው የቦክስ ከዋክብትም ሃዘናቸውን ገልፀዋል።
የታይላንድ የብሔራዊ ስፖርት ባለስልጣን ባለፈው ዓመት ባወጣው መረጃ በአገሪቱ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ከ10 ሺህ በላይ ቦክሰኞች ተመዝግበዋል።
ስፖርትን የተመለከተው የብሔራዊ ህግ አውጭ ጉባዔ ምክትል ኃላፊ ገን አዱሌኣድጂ ኢንታፖግ በበኩላቸው " ዕድሜያቸው ከ12-15 ያሉ ህፃን ቦክሰኞች መመዝገብ፤ ከቤተሰቦቻቸው ፈቃድ ማግኘት እንዲሁም ራሳቸውን ከአደጋ የሚጠብቁበት ልብስ መልበስ አለባቸው " ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ዘመቻ የሚያካሄዱ ቡድኖች ለውድድሩ አነስተኛው ዕድሜ 18 ዓመት መሆን አለበት ሲሉ ጠይቀዋል።
ከአኑቻ ሞት ቀደም ብሎ ጣላኒያዊው ቦክሰኛ ክርስቲያን ዳጊኦ በውድድር ላይ ሕይወቱ ማለፉ የሚታወስ ነው።













