ሐዘንተኛው ውሻ አሳዳጊው የሞተበት ቦታ ላይ ለ80 ቀን ያህል ጠብቆታል

Dog in road ውሻው በመንገድ ላይ ቆሞ

የፎቶው ባለመብት, Pear Video

የምስሉ መግለጫ, የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ስለ ውሻው ደህንነት ትኩረት ሰጥተው ሃሳባቸውን ሲገልፁ ነበር

ውሻ በታማኝነቱ ከእንስሳት ሁሉ የላቀ ነው ይባላል፤ ለታማኝነት ውሻን ተምሳሌት ሲደረግም ይደመጣል፤ ለዚህም በቻይና የሆነው አንዱ ማሳያ ነው።

በቻይና አንድ ውሻ አሳዳጊውን ከአራት ወራት በፊት በሞት ይነጠቃል። በአጋጣሚውም በሃዘን ልቡ ይሰበራል፤ ታማኝ ነውና እንደ እሳት የሚፈጀውን ሃዘኑን ችሎ እርሷን ካጣበት መንገድ ቁሞ መዋልን መርጧል- ትመጣ እንደሁ ብሎ።

በመኪና መንገድ ላይ ቁጭ ብሎ ለ80 ቀናት ያህል ሳይሰለች ማዶ ማዶውን እያየ መጠባበቁን ቀጠለ።

ድርጊቱ በቻይና የበይነ መረብ ተጠቃሚዎችን ቀልብ የገዛና ያሳዘነ ነበር።

ውሻው በሞንጎሊያ ሆሆት መንገድ መካከል ላይ ሆኖ የተቀረፀው ተንቀሳቃሽ ምስልም 'ሲና ዌቦ ማክሮ ብሎግ' የተሰኘ ገፅ ላይ 1.4 ሚሊዮን ጊዜ ታይቷል።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ እንደሚያሳየው ውሻው አሳዳጊው ከሞተችበት ጊዜ አንስቶ በየቀኑ መንገዱ ላይ ይታይ ነበር። በአካባቢው የሚሰራ አንድ የታክሲ አሽከርካሪም ሰዎች ውሻውን ሊረዱት ቢፈልጉም ሮጦ እንደሚያመልጥ ተናግሯል።

አሽከርካሪው "በመንገዱ የሚያልፉ አሽከርካሪዎች ምግብ ይሰጡታል፤ ነገር ግን ከመኪናው ወርደን ስናየው ጥሎት ይሄዳል" ሲል የታዘበውን አካፍሏል።

ይህም አሳዳጊዋ ከውሻው ጋር ያላት ትስስር በጣም የጠበቀና ጥልቅ እንደነበር ያሳያል፤ እርሷ ከሞተች በኋላ ትንሹ ውሻ የእርሷ ጠባቂ ሆኖ ቀርቷል።

"በየቀኑ ውሻውን መንገድ ላይ አየዋለሁ፤ በሁለቱ መካከል ያለው ፍቅር እውነተኛ እንደነበር ያስታውቃል" ይላል አሽከርካሪው።

በሐዘን የተጎዳው ውሻ ደህንነት በርካቶችን ሳያሳስብ አልቀረም ታዲያ።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ ሲና በተባለ ድረገፅ ከተለቀቀ ጊዜ አንስቶ ድረገፁ ከትዊተርና ፌስቡክ በላይ ሰዎች በውሻው ታማኝነት ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ነበር።

አንድ ሌላ ግለሰብም "ይህ ትንሽ ውሻ በጣም ታማኝ ነው ፤ ቤተሰቦቼ ውሻ ነበራቸው ፤ ሁል ጊዜም ከትምህርት ቤቱ በር ላይ ይጠብቀኝ ነበር" ሲል የራሱን ተሞክሮ ያስታውሳል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጭም "ውሻው በመንገዱ መሃል መቆሙ በጣም አደገኛ ነው፤ የሆኑ ሰዎች በማደጎ እንደሚወስዱትና እንደሚያሳድጉት ተስፋ አደርጋለሁ" ሲል የውሻው ደህንነት እንደሚያሳስበው ገልጿል።

ይሁን እንጂ ይህ አጋጣሚ በቻይና የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ ቀደም አንድ ሌላ ውሻም አሳዳጊው ከስራ ወጥቶ ወደ ቤቱ ሲሄድ የባቡር ጣቢያ ላይ ቆሞ ይጠብቀው ነበር።

በጃፓንም ከመቶ ዓመታት በፊት ባቡር ጣቢያ እየቆመ አሳዳጊውን የሚቀበል ውሻ አሳዳጊው ከሞተ በኋላም ተግባሩን ለ9 ዓመታት ቀጥሎ ነበር።