የጣና ቂርቆስ ገዳም መነኮሳትና መናኞች በእምቦጭ ምክንያት ገዳሙን ለቀው እየወጡ ነው

መነኮሳት በእምቦጭ የተያዘች ጀልባን ሲጎትቱ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian DJ FB

በደቡብ ጎንደር ዞን ገደራ ወረዳ የሚገኘውና ከጣና ገዳማት አንዱ የሆነው የጣና ቂርቆስ ገዳም መነኮሳት በእምቦጭ አረም ምክንያት ገዳሙን ለቀው እየወጡ ነው።

ከመነኮሳቱ አንዱ የሆኑት አባ ወልደመድህን ገ/ማሪያም እምቦጭ በገዳሙ ላይ ፈተና ሆኗል ይላሉ።

"መነኮሳት ከመንፈሳዊ ስራቸው ውጭ ለተግባረ ስጋቸው ስራ ይሰራሉ፤ ነገር ግን እምቦጩ ለስራቸው ተግዳሮት ሆኖባቸዋል" የሚሉት አባ ወልደመድህን የገዳሙን ጀልባም ለስራ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎታል፤ እንስሳትን ለማደለብ የሚጠቀሙበትን ሳር ይዞታል፤ ገዳሙ እንዳይጎበኝም እንቅፋት ሆኗል ይላሉ።

ገዳሙ ከባህር ዳር ከተማ በጀልባ ሶስት ሰዓት ያስጉዛል። አሁን ግን ጀልባው መጠጋት ባለመቻሉ በእግራቸው ሊጓዙ ግድ ሆኗል።

በተለይ የገዳሙ የእርሻ መሬት በአረሙ በመወረሩ ላለፉት ዓመታት ችግር ላይ እንደነበሩና ባለፈው ዓመት አሜሪካ አገር በሚኖሩ ግለሰቦች እርዳታ አረሙ ተለቅሞ አልቆ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ይሁን እንጂ በማዕበል ተገፍቶ ከሌላ አካባቢ የሚመጣው አረም እንደገና መዛመት እንደጀመረ ይገልፃሉ።

የጣና ገዳማት

የፎቶው ባለመብት, Bahir dar City Communication FB

መነኮሳቱ ገዳሙን ለቀው እየወጡ ነው የሚባለው የማይመስል ነው የሚሉት አባ ወ/መድህን የእርሻ መሬታቸው በአረሙ በመያዙ ከምዕመናኑ በምፅዋት የሚመጣ ምግብን እየተቃመሱ መቆየታቸውን ግን ተናግረዋል።

"ቅርስ ጠባቂ ነን፤ እርዱን ብለን እንማፃናለን እንጂ ፈተና ሲመጣ ጥሎ መውጣት አይቻልም። ለማን አስረክበን ነው ጥለን የምንወጣው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

የገዳሙ አስተዳዳሪ (አበምኔት) አባ ገብረፃድቅ ወልደቂርቆስ ግን የገዳሙ መውጫ መግቢያም በአረሙ መያዙን፣ ጎብኝዎች ገዳሙን ለመጎብኘት እንዳልቻሉና በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ መነኮሳቱ ሰብል ማምረት እንዳልቻሉ ጠቅሰው በእምቦጩ ምክንያት ገደሙን ለቀው የወጡ እንዳሉ ይናገራሉ።

ለገዳሙ ዕቃ የጫነች ጀልባ በእንቦጩ አረም በመያዟ ተገፍታ መውጣቷ ለገዳሙ አስተዳዳሪ የቅርብ ጊዜ ትውስታቸው ነው።

በገዳሙ የሚገኘው መንፈሳዊ ጉባዔ አባላት የገዳሙ መነኮሳት የሚያመርቱትን ይመገቡ እንደነበርና ጉባዔው በእምቦጩ ምክንያት መበተኑንም ለንግግራቸው ዋቢ ያደርጋሉ።

ቤተክርስቲያኑ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ካህናትም እየወጡ መሄዳቸውን አስተዳዳሪው (አበምኔቱ) ለቢቢሲ ገልፀዋል።

"መነኮሳት ብንሆንም በቀን አንድ ጊዜ ምግብ ያስፈልጋል፤ የጣፈጠም ባይሆን፣ ሆድም የሚሞላ ባይሆን ፤ ዋና ዓላማው ፀሎት፣ ምናኔና ታሪኩን ለትውልድ ማስተላለፍ ቢሆንም ይህን ለማድረግ ምግብ ማስፈለጉ አያጠያይቅም" ይላሉ።

ነገር ግን ከሁለት ዓመታት ወዲህ ገዳሙ ምንም ማምረት ባለመቻሉ እስካሁን በምዕመናን ድጋፍ እንደቆሙ ያስረዳሉ።

"ርሃቡንና ጥሙን ተቋቁሞ የሚቆይ እንዳለ ሁሉ አልችል ብለው የሚወጡም አሉ" የሚሉት አስተዳዳሪው (አበምኔቱ)፤ በሌላም በኩል የገዳሙንና የሐይቁን ፈተና ላለማየት፣ እንዲሁም ከግለሰብም ሆነ ከመንግስትም የሚደርስላቸው ሲያጡ በብስጭት ጥለው የሄዱ እንዳሉ ይናገራሉ።

በዚህም ምክንያት የመነኮሳትና የመናኞች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱንም ያስረግጣሉ።

ለነፍስ ያደሩ መነኮሳትና መናኞች በእምቦጭ ምክንያት ገዳሙን ጥለው እየወጡ መሆናቸው ከመንፈሳዊነቱ ጋር አይቃረንም ወይ ያልናቸው አባ ገ/ፃድቅ "መነኮሳቱ ለፈጣሪ አላድር ብለው ፤ ስጋችን ጎደለብን ብለው እየሸሹ አይደለም" ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት እየሸሹ ያሉት ወደ ከተማ አሊያም የተሻለ ነገር ፍለጋ ሳይሆን በርሃ ነው።

በመንፈሳዊ ሕይወትም ቢሆን ቁጭት አለ የሚሉት አስተዳዳሪው "ከብዝሃ ሕይወትነቱ ባሻገር የጣና ሐይቅ እነ አቡነ ሰላማ፣ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ፣ ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ የፀለዩበትና ብዙዎችን የፈወሱበት፣ ብዙ አራዊቶች በውስጡ የሚገኙበት፣ በርካታ ሰዎች ጥማቸውን የሚቆርጡበት ነው ብሎ በማሰብ ቁጭት አድሮባቸዋል" ሲሉ ያብራራሉ።

ቁጭቱ ለሌላውም ሰው የሚሰማው ቢሆንም በተለይ መሃል ሃይቁ ላይ ለሚገኙት ለእነሱ ይብሳል።

አረሙ የገዳሙን ይዞታ ሙሉ በሙሉ ወሮታል፤ በግምት 6 ሄክታር የሚሆነውን የእርሻ መሬትም ሸፍኖታል ይላሉ -አባ ገብረፃድቅ።

ገዳሙ ከሁለት ዓመታት በፊት አባቶችና እናቶች እንዲሁም የመንፈሳዊ ጉባዔ ተማሪዎችን ጨምሮ 200 መናኞች ይገኙበት የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን ቁጥራቸው ቀንሶ 165 መነኮሳት እንደሚገኙ አስተዳዳሪው ተናግረዋል።