"ለውጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ውጤት ነው" ዳዉድ ኢብሳ

በአሁን ወቅት እየታየ ያለው ለውጥ በሕዝብ ትግልና መስዋዕትነት የተገኘ ነው ሲሉ የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳዉድ ኢብሳ ቅዳሜ ዕለት አዲስ አበባ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በገቡበት ወቅት በሰጡት መግለጫ ተናገሩ።
አቶ ዳዉድ እንዳሉት ግንባራቸው ከ26 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው መንግሥት ባደረገው ጥሪ በሰላማዊው የፖለቲካ መድረክ ላይ ለመሳተፍና በሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲጠናከር በጋራ ለመስራት እንደሆነ ተናግረዋል።
በቀጣይ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድርግ ከመንግሥት፣ ከአባሎቻቸው፣ ከደጋፊዎችና ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
በረጅም ጊዜም በመላው ሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍንና ሕዝቡም በሁሉም ደረጃ በምርጫ መሪዎቹን ለመምረጥ የሚያስችል ሥርዓት በመገንባት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
በሃገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በመስራት በኩልም ኦነግ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አቶ ዳዉድ ገልፀዋል።
የኦነግ መሪዎች አዲስ አበባ መግባት
በአቶ ዳዉድ ኢብሳ የሚመራ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አባላት መስከረም 05/2011 አዲስ አበባ ገብተዋል።
ለበርካታ ዓመታት ከሃገር ውጪ የቆየው ኦነግ የትጥቅ ትግልን ለማቆም መወሰኑን ተከትሎ ነው የድርጅቱ መሪዎች ወደ ሃገር ቤት የተመለሱት።
መንግሥት የትጥቅ ትግል ለሚያደርጉትና በስደት በውጪ ሃገር ለነበሩት የፖለቲካ ቡድኖች ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ነው የኦነግ አመራር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው።
ኦነግ ወደ ሃገር ከመመለሱ በፊት ከመንግሥት ጋር የተናጠል ውይይት ለማድረግ ጠይቆ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ኤርትራ ውስጥ ንግግር መደረጉ ይታወሳል።
አዲስ አበባ ከገቡት የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች በተጨማሪ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ የቡድኑ ወታደሮች ከኤርትራ በትግራይ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
ለኦነግ አመራርና አባላት አቀባበል ለማድረግ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ በመስቀል አደባባይ ተገኝቶ ነበር።












