የሕዝብ ፍላጎት ካለ ባንዲራን መቀየር ይቻላል፡ ጠ/ሚ ዐብይ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, MICHAEL TEWELDE

ጠቅላይ ሚንስትሩ ዐብይ አህመድ ዛሬ ረፋዱ ላይ ለተወሰኑ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት በሰንደቅ አላማ ምክንያት አለመግባባትና ግጭት መፈጠር እንደሌለበት አሳስበዋል።

ባለፉት ጥቂት ወራት በተለያዩ የሃገሪቱ ስፍራዎች ዜጎች ለተቃውሞም ሆነ ለድጋፍ አደባባይ ሲወጡ የወደዱትን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ በአደባባይ መታየት የተለመደ ሆኗል።

ከወራት በፊት ለእስረ ይዳርጉ የነበሩ ሰንደቅ አላማዎች ዛሬ ሰዎች እንደፈቀዳቸው ይዘው ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።

ትናንት ረፋዱ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የፊታችን ቅዳሜ ወደ ሃገር የሚመለሱትን የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራሮችን ለመቀበል በማሰብ የኦነግ ባንዲራን በመንገዶች ጠርዥ ላይ በቀለም በሚቀቡ ወጣቶች እና እነሱን በተቃወሙ ነዋሪዎች መካከል ግጭት ተከስቶ ነበር።

ስንደቅ ዓላማን በተመለከተ እና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ''ባንዲራ የሃገር ወይም የፓርቲ የሃሳብ መግለጫ እና ማሳያ አርማ ነው። የትኛውም ቡድን ሃሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብት አለው። ይህም መብት ባንዲራን ይጨምራል'' ብለዋል።

''ያለን ተሞክሮ አንዱ አንዱን አሸንፎ ስልጣን ይዞ ገዢ መሆን እንጂ መሪ መሆን አይደለም። እንደ ማሕብረሰብ አሸንፈን አናውቅም። አሸንፈን የምናውቀው ወራሪዎችን ብቻ ነው። አሁን እኛ እያልን ያለነው፤ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ይሁን ሳይሆን ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት አውድ ይፈጠር ነው'' ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ጨምረውም፤ አሜሪካ 13 ጊዜ ባንዲራዋን መቀየሯን በማስታወስ ''የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ከሆነ ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ መልኩ መክሮ፣ ዘክሮ እና ደምጽ ሰጥቶ ባንዲራው ሊቀየር ይችላል። ለዚህ ግን ትዕግስት የሌለው ተሸናፊ ነው'' ብለዋል።

''በቀን ሁለት ጊዜ በልቶ የማያድር ዜጋ ባለባት ሃገር የህዝብን ጥቅም እንዴት እናስጠብቅ ብሎ ከማሰብ ይልቅ፤ ጉልበቱን ለማሳየት ይሚፍጨረጨር ኃይል ካለ ማንም የማያሸንፍበት እልቂት ውስጥ እንገባለን። የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሸንፍ የሚፈልግ ኃይል ሰጥቶ መቀበልን ማወቅ ይኖርበታል'' ሲሉም ተደምጠዋል።

'ሆርን ኦፍ አፍሪካ'

ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ ረፋዱ ላይ በሰጡት መግለጫ መግለጫ ላይም መተባበርና በአንድነት መቆም በኢትዮጵያዊያን መካከል ብቻ መሆን ያለበት ነገር ሳይሆን የአካባቢውን ሃገራት በማቀፍ ትስስር መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።

''ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ አንድ ላይ ብንሰባሰብ በምሥራቅ አፍሪካ ኃያል ሃገር መፍጠር እንችላለን። ለሁላችን የሚበቃ መሬት፣ ውሃ እና ነዳጅ ያለው ሃገር እንፈጥራለን። ተበታትነን ግን ተሰልፈን ቻይናን ስንለምን እንኖራለን። ህዝቡም ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሃሳቡን በመደገፍ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪዬን አቀርባለሁ።'' በማለት በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ሃገራት ተሰባስበው አንድ ኃያል ሃገር እንዲመሰረት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው አልፈዋል።