ጋዳፊ ከስልጣን እንዲወርዱ ሲደረግ በነበረ ግድያ የተሳተፉ 45 ሰዎች ላይ ሞት ተፈረደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሊቢያ ፍርድ ቤት 45 የሚሊሻ ታጣቂዎች በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ወሰነ።
የሊቢያ ፍትህ ሚኒስቴር እንዳለው 45ቱ ሚሊሻዎች የጋዳፊ መንግሥትን ለመጣል ብረት ያነገቡ አማጺያን ላይ በከፈቱት ተኩስ በርካቶችን በመግደላቸው ነው የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው።
ኤኤፍፒ እንደዘገበው ከጋዳፊ የስልጣን ዘመን በኋላ 45 ሰዎች ላይ በተመሳሳይ ጊዜ የሞት ፍርድ ሲተላለፍ ይህ ትልቁ ቁጥር ነው።
በሊቢያ ከተቀሰቀሰው ህዝባዊው አመጽ በኋላ አገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ርቋት ቆይታለች።
45 ሰዎች ላይ ከተላለፈው የሞት ፍርድ በተጨማሪ 54 ሰዎች ላይ የአምስት ዓመት የእስር ፍርድ ተላልፏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የጋዳፊ ልጅ የሆነው ሰይፍ አል-ኢስላምን ጨምሮ በጋዳፊ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የነበሩት ላይ የሞት ፍርድ ተላልፎ ነበር።
በሊቢያ የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው ፍርደኞች አብዛኛውን ጊዜ ፍርዱ ተፈጻሚ ሳይሆንባቸው እድሜ ልክ በእስር እንዲያሳልፉ ይደረጋል።
ይሁን እንጂ ሰይፍ አል-ኢስላም ከአንድ ዓመት በፊት ከእስር ተለቋል።
ሰይፍ አል-ኢስላም ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ከሬውተርስ ጋር ነበረው ቆይታ ወደ ፖለቲካው ዓለም ለመመለስ እየሰበ እንደሆነ ተናግሮ ነበር።














