ሊቢያ በ205 ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ አወጣች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ስደተኞችን ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ በህገ-ወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ 205 የሊቢያ እና የሌሎች ሃገራት ዜጎች ላይ ሊቢያ የእስር ትዕዛዝ አወጣች።
በእስር ትዕዛዙ ላይ እንደተጠቀሰው፤ 205ቱ ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች፤ ስደተኞችን በማሰቃየት፣ አስገድዶ በመድፈር እንዲሁም ነፍስ በማጥፋት የተከሰሱ ናቸው።
የሊቢያ ጠቅላይ አቃቢ ህግ እንደገለጹት የእስር ትዕዛዙ ከተቆረጠባቸው መካከል የሃገሪቱ የደህንንት ሃላፊዎች፣ በሊቢያ የሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት ኤምባሲዎች እና የስደተኞች ማቆያ ጣቢያ አለቆች ይገኙበታል።
በአውሮፓውያኑ 2011 የቀድሞ የሊቢያ መሪ ሙዓመር ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሊቢያ ከገባችበት ቀውስ መውጣት ተስኗት ትገኛለች።
ስልጣን በተለያዩ ሚሊሻዎች እና በሁለት ተቀናቃኝ መንግሥታት እጅ ስለሚገኝ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲኖሩ እድል ከፍቷል።
ከስሃራ በታች ካሉ ሃገራት ለሚመጡ ስደተኞች በቀይ ባህር አድርገው አውሮፓ ለመግባት ለሚያደርጉት ጥረት ሊቢያ ቁልፍ መሸጋጋሪያ ሃገርም ነች።
የህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎቹ መረብ ላይ ምርመራው የተጀመረው ከአንድ ዓመት በፊት ሲሆን የጣሊያን አቃቢ ህግም በምርመራ ስራው ላይ ተሳትፎ እያደረገ ነው።
የሊቢያ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ምረመራ ቢሮ ዳይሬክተር ሴዲቅ አል-ኑር እንዳሉት ከሆነ በህገ-ወጥ ስራው ላይ በርካት የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ይገኙበታል።
ከዚህ በተጨማሪም ዳይሬክተሩ እንዳሉት አዘዋዋሪዎቹ እና ጽንፈኛው ኢስላሚክ እስቴት ቀጥተኛ ግኑኘነት አላቸው።












