ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ካለሁበት 38፡ ''ሳላስበው ወደ ትምህርት ዓለሙ የመቀላቀሉን ሕልሜን አሳካሁኝ''
ስሜ ሕይወት እሸቴ አስፋው ይባላል። አሁን የምኖረው ኖርዌይ መዲና ኦስሎ ነው። እ.አ.አ በ2015 ነበር ወደ ኦስሎ የመጣሁት። ወደዚህ አገር ስመጣ ለመቅረት ሃሳቡ አልነበረኝም፤ ይሁን እንጂ በሚገርም አጋጣሚ እዚሁ ልቀር ቻልኩ።
አመጣጤ ቤተሰብ ጥየቃ ነበር፤ የዘመድ ሠርግ ለመካፈል። በደስታ መሃል አልፎ አልፎ የሚያስከፋ ዜና አይጠፋምና እዚሁ እያለሁ ኢትዮጵያ እሠራበት የነበረው መሥሪያ ቤት መዘጋቱን ሰማሁኝ።
ሁሌም የሁለተኛ ዲግሪዬን መሥራት እመኝ ነበር። ነግር ግን በኢትዮጵያ የመመረቂያ ጽሑፍ ከማዘጋጀት ውጪ በትምህርት ላይ እያሉ የስራ ልምምድ የማግኘት እድሉ በጣም ጠባብ ስለሆነ ወደ ሌላ አገር ሄጄ የመማር ፍላጎት ነበረኝ።
ወደዚህ ከመጣሁ በኋላም ወዲያውኑ አንዳንድ የትምህርት ዕድሎችን ወደ ማፈላለግ ገባሁኝ። በጣም ዕድለኛ ሆኜ በሚገርም ፍጥነት ወደ ትምህርት ዓለሙ የመቀላቀል ሕልሜን አሳካሁት።
መጀመሪያ ላይሳካ እንደሚችል ቢነግሩኝም እንኳን ኢትዮጵያ እያለሁኝ እሠራ የነበረውን ካዩ በኋላ የትምህርት ጥማቴን በመረዳት የትምህርት ዕድሉን ሰጡኝ።
ኖርዌይን ከኢትዮጵያ ምን ልዩ ያደርጋታል?
በኦስሎ መኖር ከጀመርኩኝ ሦስተኛ ዓመቴን እየጨረስኩኝ ነው። አዚህ ከመጣሁ ጀምሮ ኢትዮጵያን ከኖርዌይ ማነፃፀር ማቆም አልቻልኩም። ለምሳሌ በጣም የሚደንቀኝ ሁሉም ሕግ አክባሪ መሆናቸውና ሥነ-ሥርዓታቸው ነው።
በተለይ የሕዝብ መገልገያ ባስ በምጠቀምበት ጊዜ ፀጥታው በጣም ያስገርመኛል። እኔ የለመድኩት ጫጫታ በመሆኑ ፀጥታው ባዕድ ሆኖብኝ ነበር። ድምፃቸው በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ በመጀመሪያ ሰሞን እያወሩ መሆኑ ዘግይቶ ነበር የሚገባኝ።
እንደውም በመንገድ ላይ የሚያስደንቀኝ ነገር ደግሞ ምንም ቢገጥማቸው በትዕግስት ያሳልፋሉ እንጂ በምንም ተዓምር የመኪና ጥሩምባ አያሰሙም።
ኖርዌይ በጣም ውሃማ አገር በመሆኗ ብዙ ዓይነት የዓሣ ምርቶች አሏት። ከሁሉም ስበላው የሚያስደስተኝ ሳልመን የሚባለው ሮዝ ከለር ያለው የዓሣ ዘርን ነው።
ኖርዌይ ደረጃውን የጠበቀ የሳልመን ዘር ከማቅረቧ ባሻገር ዋጋውም ከሌላው አገር አንፃር ተመጣጣኝ ነው። ተመጣጣኝ ሲባል ግን ርካሽ ማለትም አይደለም።
በተለይ በእስያውያን 'ሱሺ' በመባል የሚታወቀው መግብ በጣም እወደዋለሁ። እንደውም ገንዘብ ቢኖረኝ በየቀኑ ብመገበው ደስ ይለኛል።
ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ እንዳስብ የሚያደርጉኝ ብዙ የሚናፍቁኝ ነገሮች ቢኖሩም አንኳን ከሁሉም በላይ የሚናፍቀኝ እንጀራ ነው። በተለይ ደግሞ ፍርፍር ሁልጊዜ ይናፍቀኛል።
ከረዥም የቀን ውሎ በኋላ ከቤቴ መስኮት ይታየኝ የነበረው ጫካ በግንባት ምክንያት ከመሸፈኑ በፊት እረፍት እና ደስታን ይሰጠኝ ነበር። አሁንም ቢሆን እንደቀደመው አይነት እይታ ባይኖረኝም በጥቂቱ ይታየኛል።
የሚያሳዝነው ግን ዊንተር የሚባለው ብርዳማው ወቅት ሲመጣ ማየት አለመቻሌ ነው። እንደው አቅሙ ቢኖረኝ የኢትዮጵያን ፀሐይ ባመጣኋት ነበር።
በዚህ በብርድ ወቅት ከቅዝቃዜው በላይ የሚገርመኝ ነገር፤ ወቀቱ እና ጭለማው መርዘሙ ነው። በ24 ሰዓት ውስጥ ለሶስት ሰዓታት ያክል ብቻ ነው ሰማዩ ፈገግ የሚለው። ከሌሊቱ 11 ሰዓት ትንሽ ብርሃን ነገር ይታይና ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ መልሶ ይጨልማል።
ኦስሎና አዲስ አበባ ይለያዩ እንጂ አልፎ አልፎ ይመሳሰሉብኛል። ከስንት አንዴ የምሄድበት ሰፈር አለ፣ ወደዚያ የምትወስደው መንገድ ደግሞ ወደ ፒያሳ የሚወሰደውን ዳገት ሁሌም ያስታውሰኛል። በተጨማሪ በእኛ መጋቢት ሲገባ አዚህ የምትወጣ አበባ አለች፣ እሷ ደግሞ መስከረም ሲገባ የምትታየውን አደይ አበባን ታስታውሰኛለች።
ስዊድንን ልውደዳት እነጂ ከባድ ጊዜያትም አሳልፌባታለሁ። ትምህርቴን መቀጠሌን ካወቅኩኝ በኋላ ባለቤቴ አብሮኝ እዚህ እንዲኖር ጥያቄ አቅርቤ ነበር። እንደተነገረኝ በተባልኩባቸው መሥሪያ ቤቶች በመሄድ አስፈላጊዎቹን ደብዳቤዎች ለማግኘት ጥያቄ አቀረብኩኝ።
በአንደኛው መሥሪያ ቤት የነበረው ኃላፊ ግን እንቅፋት እንደሆነብኝ ያህል ነበር የተሰማኝ። ደብዳቤውን በምንም ተዓምር ማግኘት እንደማልችል ነገረኝ። የእኔን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም። በጣም ያሳዘነኝ ደግሞ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ወይ ደብዳቤውን ወይም ደግሞ የመከልከያ ማስረጃ ወረቀቱን በሕጉ መሠረት መስጠት ሲገባው ሁለቱንም ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነበር።
ያኔ ባጋጣሚ የእዚህ አገር ነዋሪ የሆነ የማውቀው ሰው ስለነበር በእርሱ በኩል ጥያቄውን በተደጋጋሚ ማስገባት ነበረብኝ። አዲስ ባለትዳሮች ስለነበርን ናፍቆቱም ክፉኛ ከባድ ስለነበር የሞከርኳቸው መንገዶች ሁሉ ሳይሆኑ ሲቀሩ ተስፋ ወደ መቁረጥ እያመራሁ ነበር። ያየማውቀው ሰው ግን ያለማሰለስ እርዳታውን አበርክቶልኝ ባለቤቴ ተከትሎኝ ሊመጣ ችሏል። ያንን ጊዜ ግን እንደቁስል ነው የማየው።
ሁሉም ያልፋልና፣ ከባዱም ጊዜ አልፎ ከባለቤቴ ጋር አብረን እየኖርን፣ እኔም ትምህርቴን እየተከታተልኩና የልጆች መጽሐፍ እየደረስኩ፣ አንድ ልጅ አፍርተን እየኖርን እንገኛለን። ደስተኛ ብሆንም አንኳን እራሴን በቅስበት ኢትዮጵያ ማግኘት ብችል የወላጆቼ ቤት ውስጥ እራሴን ባገኘው ደስታውን አልችለውም።
ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገረቻት
የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦