ካለሁበት 37፡ ''አብረን ጥሩ ነገር የምንሠራበት ዕድል አልተፈጠረም''

መንግስተአብ ገብረገርግስ እባላለሁ። የምኖረው በዋሺንግተን ዲሲ በሲልቨር ስፕሪንግ ከተማ ነው። ከአራት ዓመታት በፊት ነበር ለትምህርት ወደዚህ አገር የመጣሁት።

ሲልቨር ስፕሪንግ ኢትዮጵያውያንን እና ኤርትራውያንን ጨምሮ በአሜሪካ ብዙ ስደተኞች የሚኖሩባት ከተማ ናት።

እኔ መጀመሪያ ወደዚህ ስመጣ ብዙ በረዶ የነበረበት ጊዜ ስለነበር በጣም ከባድ ነበር። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ያለ መኪና መንቀሳቀስ የማይታሰብ ነው። በዚህ ምክንያት በመጀመርያዎቹ ሁለት እና ሦስት ወራት ከቤት ወደ ትምህርት ቤት በመመላለስ ብቻ ነበር ያሳለፍኩት። አብዛኛውም ሰው ሥራ ስለሚውል ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረኝን ማህበራዊ ሕይወት እዚህ ላገኘው ባለመቻሌ ከብዶኝ ነበር።

የአሜሪካ ኑሮ ሃገር ቤት ሆነን እንደምናስበው አይደለም። መጀመሪያ ስመጣ ኢትዮጵያ እያለሁ ስሰማው እንደበር ሆኖ አላገኘሁትም። ወደ አገሬ ልመለስ ያልኩበት ጊዜም ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን የአገሪቱን አሠራር እየለመድኩት ስመጣ፣ ወንድሞቼም እዚህ በመሆናቸው በሕይወቴ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብዬ በማሰብ እዚህ እየኖርኩኝ ነው።

''አሜሪካ ራ ካልመረጥክ የምትኖርባት ካማረጥክ ደግሞ እንደ ቆሻሻ የምትጣልባት ገር''

የአሜሪካ ኑሮ እንደምናስበው አይደለም። ሁሉም ነገር በቀላሉ የሚገኝበት አገር አይደለም። ገንዘብ በብዙ ጥረት ነው የሚገኘው። አሜሪካ ሥራ ካልመረጥክ የምትኖርባት፣ ሥራ ካማረጥክ ግን እንደ ቆሻሻ የምትጣልባት አገር ናት።

እዚህ ሥራ አጥተው ኑሮ ከብዷቸው ጎዳና ላይ ወጥተው የሚለምኑ ብዙ ሰዎች አሉ። የዚህ ምክንያት አገራቸው እያሉ የነበራቸውን የአኗኗር ዘይቤ ሲያጡት አሊያም የዚህን አገር የኑሮ ሁኔታ መቀበል ሲያቅታቸው ይመስለኛል እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚፈጠረው። ሰዎችን ጎዳና ላይ ማየት ደግሞ በጣም ያሳዝናል።

ኢትዮጵያ እያለሁ ለኤፍ ኤም መቀሌ ራድዮ ጋዜጠኛ ነበርኩኝ። ከዚያ በተጨማሪም በንግድ፣ በሙዚቃ እና በትወና እሠራ ነበር።

አሜሪካን አገር በሙያዬ መቀጠል ከባድ ነው። ወደ ምፈልገው ደረጃ ለመድረስም ዝቅ ብዬ መጀመር ነበረብኝ። ይህንን መቀበል መጀመሪያ ላይ ከብዶኝ እንደነበር አልክድም።

አብረን ጥሩ ነገር የምንራበት ድል አልተፈጠረም

ሌላኛው የአሜሪካ ከባዱ ነገር ማህበራዊ ኑሮ አለመኖሩ ነው። አብዛኛው ሰው በዕለት ተዕለት ሕይወቱ የተጠመደ ነው። እኔ ግን አጋጣሚ ሆኖ እንደመጣሁ ከሁለት ወራት በኃላ 'አያ ማህበር' የሚባል ማህበር በዋሺንግተን ዲሲ ተቀበለኝ። ይህ ማህበር በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች በየዓመቱ ጉዞ በማድረግ የሚመካከሩበት እና እንደ በዓል የሚያዩት ነው።

በዚህ መድረክ ትምህርት ቤት አብረውኝ የተማሩ እና አስተማሪዎቼን ያገኝሁበት አጋጣሚ ነበር።

በአሜሪካ ምንም እንኳን እንደነዚህ ዓይነት ማህበሮች ቢኖሩም አጋጣሚዎች ከሌሉ የሚፈለገውን ያህል ግን ሕብረት የለም። እነዚህ ማህበራት በሰሜን አሜሪካ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ እንድንገናኝ መድረክ ቢያዘጋጁም፤ ከመዝናናት እና ብር ከማዋጣት ውጪ ባለፈ ዓላማው አይገባኝም።

በኢትዮጵያና በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ ኤርትራውያን ወንድሞቻችን በስደት ሆነው የሚሠሩት የጥበብ ሥራዎች ሳይ መንፈሳዊ ቅናት ያድርብኛል። እዚህ አገር የምንኖር ኢትዮጵያውያን አብረን የምንሠራበት ጥሩ ዕድል አልተፈጠረም።

አሁን ፒዛ ቦሊዝ በሚባል የ'ፒዛ ስቶር' ውስጥ ነው የምሠራው። ይህ ድርጅት በዲሲ እና አካባቢው ከሰማንያ አምስት በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ነው። የፒዛችን ስም ደግሞ 'ፒዛ ቦሊስ' ነው።

ዝቅተኛ ሊባል የሚችል ሥራ ሰርቼ ነው እዚህ የደረስኩት። ከአሁን በፊት ኢትዮጵያ እያለሁ ፒዛ እንዴት እንደሚሠራ እንኳን አላውቅም ነበር። አሜሪካ ብዙ ሙያ የምታስተምር አገር በመሆኗ ከዚህ በፊት ሠርቼው የማላውቀውን የፒዛ ሥራ ተያያዝኩት።

የምኖርበት አካባቢ የመኖሪያና የሥራ ቦታ በመሆኑ አብዛኞቹ እንደ ባህር ዳርቻ ያሉ ተፈጥሯዊ የመዝናኛ ቦታዎች ከዲሲ እና አካባቢዋ ወጣ ብለው ነው የሚገኙት። ከዚያ ውጪ ግን ፓርክላንድ የሚባል የመዝናኛ ቦታ አሉት።

ፓርክላንድ እንደ ቴንስ፣ ቮሊቦል እና የኳስ ሜዳ መጫወቻ ስፍራዎች አሉት። እናም አልፎ አልፎ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጓዶኞቼ ጋር የምጫወታቸው ነገሮች ትዝ ሲሉኝ ወደዚህ የመዝናኛ ቦታ በመሄድ እራሴን አዝናናለው።

የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት የተገደበ ነው

ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኛ በነበርኩበት ጊዜ ጎን ለጎን አዳዲስ ነገሮች መሞከር እወድ ነበር። ይህ ደግሞ እዚህ በጣም ረድቶኛል። በእርግጥ ጋዜጠኝነት እና የፒዛ ነጋዴ መሆን የሚገናኙ አይደሉም። ዕድሎች ሲጠፉ ግን ሕይወት መቀጠል ስላለባት በሌላ ዘርፍ ገብቼ በመሥራት ላይ ነኝ።

ለጋዜጠኝነት ልዩ ፍቅር ነው ያለኝ። በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ሙሉ በሙሉ ለሕብረተሰብ ለመሥራት ስታስብ ግን ብዙ የሚገድቡህ ነገሮች አሉ። መሥራት የምትፈልጋቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ብዙ ፈተናዎች ይጋረጡብሃል። እዚህ ሃገር ካለው የጋዜጠኝነት ሽፋን በጭራሽ የሚገናኝ አይደለም።

በሙያው ብዙ የማልረሳቸው ትዝታዎች አሉኝ። በተለይም ዓመት በዓል ሲመጣ ጋዜጠኛ ከቤተሰቦቹ ተለይቶ ከአድማጮቹ ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ ነው የሚበዛው።

ላማ የሚከፈል መስዋትነት

ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ለጥበብ ልዩ ፍቅር ስለነበረኝ በተለያዩ ክለቦች የትወና፣ ፀረ-ኤድስ እና የሚኒ ሚድያ ክለቦች እሳተፍ ነበር።

አሁን ሕይወቴን መስመር በማስያዝ ላይ ነኝ። ቀጥዬ ወደ ሃገሬ ተመልሼ የፕሮሞሽን ድርጅት በመክፈት በጣም በምወዳቸው የጋዜጠኝነት እና የፊልም ሙያ በትግርኛ ቋንቋ ከሌሎች የጥበብ ባለሞያዎች ጋር በመሆን ለሕብረተሰቡ ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችል ሥራ ለመስራት ዕቅዱ አለኝ።

በአሁኑ ሰዓት ካለሁበት እራሴን በቅጽበት ወደ ኢትዮጵያ መላክ ብችል ተወልጄ ባደኩባት፣ ወደ ውቧ ከተማ መቀሌ ልኬ እራሴን ከምወዳቸው ቤተሰቦቼ እና ፍቅረኛዬ ጋር ባገኘው ምንኛ ደስ ባለኝ።

ለላየን ፅጋብ እንደነገራት