ካለሁበት 14፡ "ብርዱ ሲከፋ፣ ቀኑም ሲያጥር የሀገሬ አየር በስንት ጣዕሙ እላለሁ።"

መባ ታደሰ

የፎቶው ባለመብት, Meba Tadesse

መባ ታደሰ እባላለሁ፤ በእንግሊዝ የኦክስፎርድ ከተማ ነዋሪ ነኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ የትምህርት ዕድል ወዳገኘሁባት ለንደን ነበር የመጣሁት፤ የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴንም እዛው አጠናቅቄ ለአስር ዓመታት ቆይቻለሁ።

ከዚያ በኋላ ግን ለንደን ሥራ የማግኘት ዕድሉ አስቸጋሪ ሆነ፤ እኔም ሌሎች አካባቢዎችን ማየት እፈልግ ስለነበር ከለንደን ወደ ኦክስፎርድ መጣሁ።

አሁን እዚህ ከመጣሁ 4 ዓመት ሆኖኛል።

ኮርፑስ ክሪስቲ በሚባል የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጥላ ሥር በሚገኝ ኮሌጅ ውስጥ በኮንፈረንስ አስተዳዳር ክፍል ውስጥ እሠራለሁ፤ ኃላፊነቴም የዩነቨርሲቲ ኮሌጁን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ የውጭ ደንበኞችን ማገናኘትና ከተማሪዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ማስተባበር ነው።

እዚህ በመጣሁበት ወቅት የቢሮ ፖለቲካውንና አሠራሩን ለመረዳት ትንሽ ጊዜ ፈጅቶብኝ ነበር ግን በሂደት ሁሉንም ነገር ተላመድኩት።

ባለሁባት ኦክስፎርድ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቱ ጥራት ስላለው ሰፊ የተማረ ማህበረሰብ አላት። ከተማዋም ሀገሪቱ በከፍተኛ ትምህርት ከፍተኛ ቦታ ላይ እንድትደርስ ጉልህ ሚና ትጫወታለች።

እዚህ ከመጣሁ ጀምሮ ሁልጊዜም የሚገርመኝ በነዋሪዎች መካከል ያለው ሰፊ የኑሮ ልዩነት ነው።

መመገቢያ ቦታ

የፎቶው ባለመብት, MEBA TADESSE

እኔ በምሠራበት ኮሌጅ እንኳን መካከለኛ ገቢ ባላቸውና በባለፀጎቹ መካከል የሚታየው የአኗኗር ዘይቤ ከኛ በጣም የተለየ ነው ለምሳሌ አስተማሪዎች አንዳንዴ በብር ማዕድን በተሠሩ ማንኪያዎችና ሹካዎች ሲመገቡ አያለሁ ፤ ይሄ ልዩነት ሁሌም ያስገርመኛል።

በዚህ ከተማ አቅም ኖሮኝ አንድ ነገር መለወጥ ብችል የሥራ ዕድሉን ለሁሉም ተወዳዳሪ አደርገው ነበር። ምክንያቱም እዚህ ብዙ ጊዜ የሥራ ዕድል የሚያገኙት ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ተማሪዎች ናቸው፤ ስለዚህ የገበያ ውድድሩ ፍትሐዊ እንዲሆን ሁሉንም የሚያቅፍ የሥራ ዕድል እፈጥር ነበር።

በእርግጥ ኦክስፎርድ በጣም ትንሽ ናት ግን ሁልጊዜም የአዲስ አበባዋን ፒያሳ የማስታውስበት ቦታ አለ።

ፒያሳ

የፎቶው ባለመብት, MEBA TADESSE

ምክንያቱም የከተማዋ ዋነኛ የንግድ ቦታ ትንሽ ትርምስ ይበዛዋል መንገዱ ጠቦ መኪኖች ለማለፍ ይቸገራሉ። ያንን ሳይ ሁሌም ሀገር ቤት ይመልሰኛል።

ሁልጊዜም ቢሆን ከኢትዮጵያ የሚናፍቀኝ ነገር አየሩ ነው፤ አየሩ ቀለል ያለና ደስ የሚል ነው ፤ ብርዱም ሆነ ሙቀቱ የከፋ አይደለም፤ እዚህ ግን ብርዳማው ጊዜ በጣም እየረዘመ፣ በጋውንም ቀኑ እያጠር ሲሄድ የሀገሬ አየር በስንት ጣዕሙ እላለሁ።

እዚህ ካለው ነገር ደግሞ በቤቴ መስኮት አሻፍሬ የማየው የኮሌጆቹና ዩኒቨርሲቲዎቹ ዕይታ በጣም ይመስጠኛል፤ ረዥም ዓመት የ400 እና የ500 ዕድሜ ያላቸውና በጣም የሚማርኩ ናቸው፤ ይህን በየጊዜው በማየቴ ዕድለኛ እንደሆንኩ አስባለሁ።

ኦክስፎርድ ዪኒቨርሲቲ

የፎቶው ባለመብት, MEBA TADESSE

ሌላው እዚህ በጣም የምወደውና ደስ ብሎኝ የምበላው የታይላንድ ምግብ 'ታይ ግሪን ከሪ' ይባላል።

በስጋ፣ በዶሮም ሆነ በባሀር ውስጥ ምግቦች መሠራት የሚችል ጣፋጭ ምግብ ነው፤ ቤቴም ቢሆን ብዙ ጊዜ አብስለዋለሁ።

በቅጽበት ወደ አንድ የሚያስደስተኝ ቦታ መሄድ ብችል እራሴን ድሬዳዋ ባገኘው ህልሜ ነው።

ሕፃን ሆኜ ነው የሄድኩት ግን ሰዉ ተቀባይ መሆኑና የአየሩ ሞቃታማነት ይመቸኛል።

Presentational grey line

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገራት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦