ማንቸስተር ሲቲ በሀላንድ ሁለት ግቦች ታግዞ አሁንም “አስፈሪ” ቡድን መሆኑን አስመሰከረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኬቪን ደ ብሩይነ ተመልሷል። ፊል ፎደን ድንቅ ብቃት ላይ ነው የሚገኘው። አሁን ደግሞ ኧርሊንግ ሀላንድ ጎል ማስቆጠር ጀምሯል። ማንቸስተር ሲቲን የሚያቆመው ማነው?
ያለፈው የውድድር ዘመን ዋንጫ አሸናፊዎቹ ማንቸስተር ሲቲዎች ለሳምንታት ወደ አቋማቸው ለመመለስ ሲዳክሩ ነበር።
ሆኖም የፊት መስመሩ ባለ ግርማ ሞገስ አጥቂ ከጎናቸው አልነበረም።
ሀላንድ ባለፉት የታኅሣሥ እና ጥር ወራት በጉዳት ምክንያት አልተሰለፈም። ስለዚህም ቡድኑ ባደረጋቸው 419 ደቂቃዎች የፕሪሚዬር ሊግ ግብ አላስቆጠረም።
ኖርዌያዊው አጥቂ ወደ እንግሊዝ ከመጣ በኋላ እንዲህ የግብ ድርቅ አጋጥሞት አያውቅም።
ይህ ሁሉ ቅዳሜ ከኤቨርተን ጋር በነበረው ጨዋታ ተቀይሯል። ሁለት ግቦች ከማስቆጠሩም በላይ ቡድኑ የሊጉ አናት ላይ ወደ ተቀመጠው ሊቨርፑል እንዲጠጋ አስችሏል።
ከአንድ ሰዓት ለበለጠ ጊዜ የኤቨርተን የተከላካይ መስመር የኤቲሀድ ስታድየምን ጭር አድርጎት ነበር። የኤቨርተን ተከላካዮች ሀላንድ ወደ ግባቸው እንዲጠጋ አልፈቀዱለትም።
71ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሀላንድ ያገኘውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ኳስ ከመረብ ከማዋሃድ ወደኋላ አላለም።
“ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የነበረን ጥምረት መልካም ነበር። ደግሞ ሀላንድ ተመልሷል። ይህን ተጫዋች ይዘን ከማዕዘን ምት የመጣ ኳስ አለመጠቀም ከባድ ነው። አጨራረሱ ደግሞ ሲያምር” ይላል አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ።
ቤልጂየማዊው አማካይ ኬቪን ደ ብሩይነ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይረው ከገቡ ተጫዋቾች መካከል ነው። ሀላንድ ሁለተኛውን ግብ እንዲያስቆጥር አመቻችቶ ያቀበለው እሱ ነው።
ነገር ግን የእግር ኳስ ተንታኞችን ያስደነቀው የመጀመሪያው ጎል ነው። አጥቂው የተቃራኒ ቡድን መረብ አካባቢ ኳስ ካገኘ እንደማይምር ያሳየበትም ነው ይላሉ።
ሀላንድ በ50 የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች 52 ጎሎች አስቆጥሯል።
ልክ እንደሌሎች ክለቦች ኤቨርተንም ሀላንድን ለበርካታ ደቂቃዎች ዝም ማሰኘት ችሎ ነበር። ነገር ግን ጨዋታው ሲጠናቀቅ ይህ ዕቅዳቸው እንዳልሰመረ ገብቷቸዋል።
“ለዚህ ነው አደገኛ አጥቂ ነው የምንለው” ሲሉ የኤቨርተኑ አሠልጣኝ ሾን ዳይሽ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሀላንድ ምንም እንኳ 76 ቀናት ግብ ሳያስቆጥር ቢቆይም፣ ከሊቨርፑሉ ሞሐመድ ሳላህ ጋር የሊጉን ኮከብ ጎል አስቆጣሪነት ሰንጠረዥን እየመራ ነበር።
አሁን ግን ይህን ሰንጠረዥ በ16 ጎሎች ብቻውን ተቆጣጥሮታል።
ምንም እንኳ እንዳለፈው የውድድር ዘመን 36 ጎሎች ያስቆጥራል ማለት ባይቻልም ማንቸስተር ሲቲ ለሁለተኛ ጊዜ ሦስት ግዙፍ ዋንጫዎችን እንዲያነሳ ሊያግዝ እንደሚችል ብዙዎች ይገምታሉ።
ኧርሊንግ ሀላንድ ባለፈው የውድድር ዓመት በሁሉም ውድድሮች ለሲቲ 52 ጎሎች አስቆጥሯል።
ሲቲ በሁሉም ውድድሮች ያለፉትን 10 ጨዋታዎች አሸንፈዋል። ቅዳሜ አመሻሹን ሊቨርፑል በርንሊን አሸንፎ የሊጉን አናት እስኪቆጣጠር ድረስ ሰንጠረዡን እየመሩም ነበር።
ሲቲ በኤፍ ኤ ዋንጫ ውድድር በያዝነው ወር መገባደጃ ከሉተን ሲገጥም፤ በቻምፒዮንስ ሊጉ ደግሞ ማክሰኞ ከኤፍሲ ኮፐንሀገን ይገናኛል።
የእንግሊዝ ሊግ ፕሪሚዬር ሊግ ሊጠናቀቅ አራት ወራት ይቀሩታል። ሲቲ ከጊዜ ጊዜ እየጠነከረ መጥቷል።












